በሊባኖስ ይኖሩ የነበሩ 94 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ይመለሳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሊባኖስ ይኖሩ የነበሩ 94 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ይመለሳሉ
አዲስ አበባ መስከረም 8/2013 (ኢዜአ) በሊባኖስ ይኖሩ የነበሩ 94 ኢትዮጵያውያን በዛሬው እለት ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ተገለጸ።
በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል ጽህፈት ቤት እንደገለጸው 94 ኢትዮጵያዊያን በዛሬው እለት ወደ አገራቸው ይመለሳሉ።
ዛሬ የሚመለሱት ዜጎች የጉዞ ሰነድና የመውጫ ቪዛ በማጠናቀቅ ወደ አገራቸው ለመመለስ በዝግጅት ላይ ከነበሩ 148 ኢትዮጵያውያን መካከል ናቸው።
ተመላሾቹ በሊባኖስ እስር ቤቶች የነበሩ፣ ሆስፒታል ህክምናቸውን ሲከታተሉ የነበሩ፣ በቤይሩት ወደብ ፍንዳታ መጠለያ ያጡና ችግር ላይ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል።
በአሰሪዎች በደልና የመብት ጥሰቶች፣ የአካልና የስነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው እና መጠለያና ምግብ ያጡ ናቸውም ተብሏል።
የቆንስላ ጄነራል ጽህፈት ቤቱ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር እንዲሁም ሌሎች ድጋፍ የሚያደርጉ በጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በማስተባበር የአውሮፕላን ቲኬት ወጭዎችን እና ሌሎች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የጉዞ ሰነዶቻቸውን፣ የመውጫ ቪዛና መሰል ጉዳዮችን ማጠናቀቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ማህበር በመጠለያ፣ በህክምና፣ በኮሮናቫይረስ ምርመራ፣ አልባሳት፣ ምግብና መጠጦች፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችና የእጅ ማጽጃ ኬሚካል (ሳኒታይዘር) ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።
እኛ ለኛ በስደት የተሰኘ በሊባኖስ የሚገኝ ቡድን የመጠለያ አገልግሎት፣ የቲኬት ወጭዎችንና ሌሎችንም የተለያዩ ድጋፎችን ያደረገ ሲሆን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትም (አይኦኤም) በተመሳሳይ የአውሮፕላን ቲኬት ወጭዎችን የሸፈነ ሲሆን ሌሎች ድጋፎች ለኢትዮጵያውያኑ አድርጓል።
የሊባኖስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለ32 ኢትዮጵያዊያን የመጠለያ አገልግሎት መስጠቷም እንዲሁ።
ቆንስላ ጄነራል ጽህፈት ቤቱ ለ148 ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ የጉዞ ሰነድና የመውጫ ቪዛዎችን ያጠናቀቀ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 27 ኢትዮጵያዊያን በአሰሪዎችና በግለሰቦቹ በራሳቸው የአውሮፕላን ቲኬት ወጭ ወደ አገር ቤት ቀደም ሲል መመለሳቸው ታውቋል።
የ74 ኢትዮጵያውያን ተመላሾች የአውሮፕላን ቲኬት ወጭ የተሸፈነው በእኛ ለኛ በስደት የድጋፍ ማህበር ሲሆን የ47ቱ ደግሞ በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ነው።
ዛሬ ማምሻውን 27 ወደ አገር ቤት የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን ሽኝት እንደሚደረግላቸው ተገልጿል።
ጽህፈት ቤቱ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን በመርዳት ድጋፍ ያደረጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላደረጉት ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።