ቀጥታ፡

ማህበሩ በሱሉልታ ከተማና አካባቢዋ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚውል ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6/2013(ኢዜአ) ኔስሌ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በሱሉልታ ከተማ እና አካባቢው ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

የገንዘብ ድጋፉ በሱሉልታ ከተማና በአካባቢዋ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ 1ሺህ100 ቤተሰቦች የውሃ ስነ-ንፅህና እና ጤና አቅርቦት እንዲያገኙ የሚያግዝ መሆኑ ተመልክቷል።

ይህም የምንጭ ውሃዎችን በማጐልበት ማህበረሰቡና እንስሳት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ በአካባቢው የቦሳካ ምንጭ ውሃን በተሻለ የማጎልበት ሥራ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የገንዘብ ድጋፉ የአካባቢውን የውሃ ኮሚቴና የጤና በጐ አገልግሎት ፈቃደኞች አቅምን ለማጎልበት እንደሚውል ነው የተገለጸው።

በከተማው ስለ ወረርሽኙ መከላከያ ዘዴዎች እና የአካባቢ እና የግል ንፅህና አጠባበቅ አስመልክቶ እየተደረገ ያለውን የማሕበረሰብ ንቅናቄ ዘመቻን ለማገዝ ድጋፉ እንደሚውል ተናግሯል።

የኔስሌ የአፍሪካ ቀንድ ክላስተር ሥራአስኪያጅ አቶ ወሰንየለህ ሺፈራው እንዳሉት ድጋፉ ኮሮናቫይረስን በመከላከል ሂደት በከተማዋ በውሃና ስነ -ንፅህና ዙሪያ እየተሰራ ያለውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ታስቦ የተደረገ ነው።

ማህበሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላክል ከኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጎን በመቆም ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ለዚህም ከዚህ በፊት የጤና ባለሙያዎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ  ማህበሩ 500 እስክራብ እና  500 ጫማዎችን ድጋፍ ማድርጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።  

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አቶ አበራ ሉሌሳ በበኩላቸው ኔስሌ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር በመረዳት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይ በአካባቢው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚሰሩ ሥራዎችም በአጋርነት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

"የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኮሮናቫይረስ መከሰት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ነው" ብለዋል።

በቅርቡ በአፋር ክልል ፣ በመተሃራና  በአዋሽ አካባቢ በጎርፍ አድጋ ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖች ማህበሩ ፍጥኖ በመድረስ ድጋፍ ማድረጉን የጠቆሙት አቶ አበራ፣ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ  እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

ኔስሌ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2006 በአዲስ አበባ የተቋቋመ ሲሆን የኔስሌ አፍሪካ ቀንድ ዋና መስሪያ ቤት ሆኖም በማገልግል ይገኛል።

ማህበሩ በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ገበያዎች ውስጥ የኩባንያውን ምርቶች የማስተዋወቅ እና ገበያ የማስፋፋት ሥራ የሚሰራ ሲሆን የአፍሪካ ቀንድ ክላስተር የተለያዩ የኩባንያው ምርቶችንም በማስመጣት እንዲከፋፈሉ ያደርጋል ተብሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም