ተቋማቱ ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚውሉ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚውሉ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አዲስ ፣መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) የግል ተቋማትና ምዕመናን ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚውል ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የህክምና መሳሪያና መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተረክበዋል።
በጀርመን ፍራንክፈርት ሐመር ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን፣ የኔታቤት የህጻናት የቴሌቪዥን ፕሮግራም ባለቤት፣ ያራ ዳሎልና ፒዩር ውድ የግል ኩባንያዎች ናቸው ድጋፉን ያደረጉት።
ድጋፉ ኮቪድ-19 በአገር ደረጃ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል፣ ለመቆጣጣርና የህክምና ባለሙያዎችን ከጉዳት ለመታደግ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
በጀርመን ፍራንክፈርት ኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተወካይ ብጹዕ አቡነ ናትናኤል እንዳሉት፤ ምዕመናኑ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የህክምና መመርመሪያ መሳሪያ ድጋፍ አድርገዋል።
መሳሪያው ከኮቪድ-19 ጋር በተገናኘ ምርመራ ለማድረግ የሚያግዝ ሲሆን መሳሪያው ኮቪድ ቢጠፋም ለሌሎች በሽታዎች መመርመሪያነት የሚውል ነው።
ቤተ ክርስቲያኗ ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር በጸሎትና በጾም ምዕመናኑ እንዲተጉ በማስተማር የራሷን አስተዋጽኦ ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።
በቀጣይም የወረርሽኙ ስርጭት እስከሚያቆም ምዕመናንን በማስተማርና ድጋፍ በማድረግ ሃላፊነቷን እንደምትወጣ አረጋግጠዋል።
የየኔታ ቤት የህጻናት የቴሌቪዥን ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሃንስ ዘርፉ እንዳሉት፤ ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚውል 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አበርክተዋል።
ከድጋፉ ባሻገር ህጻናት ኮቪድ-19ን እንዴት መከላከል እንዳለባቸው ዓለም ዓቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማጋራት ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ያራ ዳሎልና ፒዩር ውድ የግል ኩባንያ ስራ አስኪያጆችና ተወካዮች ለህክምና ባለሙያዎች የሚውል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ድጋፍ አድርገዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ኮቪድ-19ን ለመከላከል በተደረገው አገራዊ ጥሪ በርካቶች ድጋፍ አድርገዋል።
ዛሬ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ዶክተር ሊያ፤ ''ቫይረሱን ለመከላከልና የህክምና ባለሙያዎችን ከጉዳት ለመጠበቅ እገዛው ከፍተኛ ጥቅም አለው'' ብለዋል።
በቀጣይም የቫይረሱ ስርጭት እስሚያቆም ተቋማት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዶክተር ሊያ ጥሪ አቅርበዋል።