ቀጥታ፡

የአባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው ሰከላ 'የዓለመ ዕፅዋት የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት' ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) የአባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው ግሽ አባይ 'የዓለመ ዕፅዋት የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት' በተሰኘው የተራቆቱ ሥፍራዎችን በደን የመሸፈን መርሃ ግብር ሊተገብር መሆኑን የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚሆነው ባሳለፍነው ሣምንት በይፋ ከተጀመረው የላልይበላ የዓለመ ዕፅዋት የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት ቀጥሎ መሆኑ ተጠቁሟል።

የተራቆቱ የላልይበላ ዙሪያ ገባ ተራሮችን ወደ አረንጓዴነት ለመለወጥ ያለመ ፕሮጀክት ባሳለፍነው ሣምንት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

'ዓለመ ዕፅዋት የማደጎ ዛፍ' የተሰኘው ፕሮጀክት ማንኛውም ዛፍ በማደጎ መንከባከብ የሚፈልግ ሰው ወይም ድርጅት በአካልም ሆነ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ አንዲት ዛፍ ተክሎ ተንከባካቢ ቀጥሮ የሚያሳድግበት ሥርዓት ነው።

ፕሮጀክቱ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በበይነ መረብ መትከል የሚችሉበት ሥርዓትም ይኖረዋል።

በላስታ ላልይበላ ተራሮችን አረንጓዴ (ዕፅዋት) ለማልበስ የተጀመረው 'ዓለመ ዕጽዋት ማደጎ ዛፍ' ፕሮጀክት ወደፊትም በዓለም ቅርስነት በተመዘገቡ ታሪካዊ ሥፍራዎችና በአዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

ከነዚህም መካከል በቀጣይ የአባይ ወንዝ መነሻ በሆችው 'ግሽ አባይ' ላይ ሌላ የ'ዓለመ ዕጽዋት ማደጎ ዛፍ' ፕሮጀክት ለመተግበር ማቀዱን የአማራ ክልል የማኅበራት ዘርፍ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የአባይ ወንዝ መነሻ የሆነው የግሽ አባይ አካበቢ በመራቆቱ ከላልይበላ ቀጥሎ የ'ዓለመ ዕጽዋት ማደጎ ዛፍ' ፕሮጀክት እንደተሚተገበርበት ጠቁመዋል።

ከመጀመሪያው የላልይበላ ፕሮጀክት የተገኘውን ልምድ በመያዝ የጮቄ ተፋሰስ አካል የሆነውን የሰከላ አካባቢ አረንጓዴ ማልበስ እንደሚቻልም ገልጸዋል።


በላልይበላ ላይ መጀመሩ ከተማዋ የቱሪስት ከተማ በመሆኗ ቱሪስቶች በቦታና በጊዜ ሳይገደቡ ችግኝ በመትከል ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ያላቸውን ትሥሥር እንዲያጠናክሩ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

''በኮቪድ-19 ሳቢያ ወደ ላልይበላ መምጣት ያልቻሉ ጎብኚዎች ይህን ዕድል እንዲጠቀሙ ለማድረግ ያግዛል'' ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በቱሪዝም ላይ ብቻ ለተንጠለጠለው የአካባቢው የሥራ ዕድል አማራጭ ከመጨመር ባለፈ አካባቢው ለጉብኚዎች ምቹ መዳረሻ እንዲሆን ለማድረግ የጎላ ሚና እንዳለው ዶክተር ሙሉነሽ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም