ቀጥታ፡

ዓለም ባንክ በአነስተኛ የግብርና ሥራ ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች 80 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) ዓለም ባንክ በኢትዮጰያ አነስተኛ ግብርና ለሚያከናውኑ አርሶ አደሮች የሚውል 80 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን አስታወቀ።

ባንኩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የባንኩ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሮች ቦርድ በውሳኔው ላይ የደረሰው ድጋፉ የአርሶ አደሮቹን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግና የገበያ ዕድሎችን ለማመቻችት እንዲውል በማሰብ እንደሆነ ተገልጿል።

ድጋፉ ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን እምቅ አቅም አሟጣ እንድትጠቀም የሚያግዝና ነባር የዘርፉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚረዳ መሆኑም ተመልክቷል።

መግለጫው የባንኩን የ2019 እ.አ.አ የኢትዮጵያ የድህነት ሁኔታ ዳሰሳ ጠቅሶ እንደሚያመለክተው ላለፉት አሥር ዓመታት የግብርናው ዘርፍ ድህነትን በመቀነስ በኩል ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

በተጨማሪም ለሁለተኛው ዙር የግብርና ዕድገት ፕሮጀክት የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ ለሌላኛው የግብርና ዘርፍ ዕድገት ማምጫ እንደሆነ ተገልጿል።

የባንኩ ከፍተኛ የግብርና ባለሙያ ቪካስ ቹድሓሪ ተግባራዊ የተደረገው ሁለተኛው ዙር የግብርና ዕድገት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ሁነኛ በሆነ መልኩ ድህነትን መቀነስ አስችሏል።

ምርታማነትን መጨመርና አርሶ አደሮችን የመስኖ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ፕሮጀክቱ ተጨባጭ ለውጦች ካስገኘባቸው መስኮች መካከል እንደሆነም ገልጸዋል።

በዚህም ፕሮጀክቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ ከዚህ ውስጥ 37 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በአነስተኛ የግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከ254 በላይ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋላቸውን ባለሙያው ገልጸዋል።

ለዚህ ፕሮጀክት ከ2 ሺህ 600 በላይ አዳዲስና ማሻሻያ የተደረገባቸው ነባር አነስተኛ የመስኖ ልማት ቦዮች ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን እነዚህም በጠቅላላው ከ23 ሺህ በላይ ሄክታር ማልማት ያስችላሉ።

የባንኩ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኦስማኔ ዲኦኒ 45 በመቶ ግብዓት የሚያስገኘውና 80 በመቶ የሰው ኃይል የያዘው ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወሳኝ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ እስካሁን አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም ዘርፉ ብዙ ችግሮች ያሉበት ከመሆኑ አንፃር በቀጣይ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።

አሁን የተደረገው ድጋፍ ባልተገመተ የዋጋ ንረት ምክንያት የሚያገጥሙ ችግሮችን ለማቅለልና የተጓተቱ የግብርና ፕሮጀክቶችን ለመጨረስም ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በሁለተኛው ዙር የግብርና ዕድገት ፕሮጀክት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን አነስተኛ ግብርና የሚያካሄዱ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ በስምንት ክልሎች በሚገኙ 167 ወረዳዎች እየተተገበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም