ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ የመንግሥትንም ሆነ የፖለቲካ ፖርቲዎችን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ያስቀራል - ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ የመንግሥትንም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ብዙሃን መገናኛዎች ሀሳባቸውን በነፃነት ለማንጸባረቅ እንደሚያስችላቸው ባለሙያዎች ገለጹ።

ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ለኢዜአ እንዳለው፣ በኢትዮጵያ የብዙሃን መገናኛ ታሪክ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ጎልቶ ይታይ ነበር።

የብዙሃን መገናኛ ተቋማት የመንግሥትን ፍላጎት ብቻ ካላንጸባረቁ ጋዜጠኞችን በሽብር በመክሰስ ማሰር እንዲሁም ሚዲያው በገንዘብ እጥረት ከገበያ እንዲወጣ ማድረግ የተለመደ የመንግሥት አሰራር ሆኖ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ የብዙሃን መገናኛ ተቋማት ከልማታዊ ጋዜጠኝነት ውጭ ሌላ አማራጭ እንዳይጠቀሙ በሰነድ ክልክላ ይደረግ እንደነበር ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ ለብዙሃን መገናኛ ተቋማት መቀጨጭና በዕድገታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ የነበረው የፖሊሲ አለመኖር መሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የመንግሥትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት በመከላከል ብዙሃን መገናኛ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው መሥራት የሚችሉበት የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ እንዲወጣ መደረጉን ዶክተር ጌታቸው ገልጸዋል።

"ፖሊሲው ከሌሎች ሕጎች ጋር የተጣጣመና የብዙሃን መገናኛ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ የሚያስችል ከመሆኑ በተጨማሪ ሲሳሳቱ ተጠያቂ እንዲሆኑም ያደርጋል" ብለዋል።

ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱ በበኩሉ በኢትዮጵያ ብዙሃን መገናኛ እንደ አንድ ኢንዱስትሪ አለመታየቱና ሀሳብን በነፃነት መግለጽ የመንግሥት ችሮታ ተደርጎ ሲቆጠር መቆየቱን ገልጿል።

"በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥራ ላይ እንዲውል የተደረገው ፖሊሲ ገለልተኛ በመሆን ሀሳብን በነፃነት መግለጽ የማንም ችሮታ ሳይሆን መብት እንደሆነ ያረጋግጣል" ብሏል።

ባለሙያዎቹ አክለውም መንግሥት ወይም ፖለቲከኞች እጅ በመጠምዘዝ የብዙሃን መገናኛዎች የራሳቸው ፍላጎት ማንጸባሪቂያ መሣሪያዎች እንዳያደርጓቸው ፖሊሲው ክልከላ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲው ፍትሐዊ የሆነ የማስታወቂያ ገቢ እንዲኖር፣ ተቋማት በዘርፉ ባለሙያዎች እንዲመሩ እንዲሁም ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ አጋዥ መሆኑንም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

ጋዜጠኛ ጥበቡ "ፖሊሲው ሥራ ላይ ሲውል በራሳቸው የሚተማመኑ ጠንካራ የብዙሃን መገናኛ ተቋማት መፍጠር ያስችላል" ብሏል።

እንደ ጋዜጠኛ ጥበቡ ገለጻ ፖሊሲው አዋጆችና መመሪያዎች ወጥተውለት በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ ሁሉም በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል።

የብዙሃን መገናኛ ተቋማትም ሁሉንም ነገር ከመንግሥት ብቻ ሳይጠብቁ ለዘርፉ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም