በአማራ ደቡብ ወሎና ትግራይ ምዕራባዊ ዞኖች ለ385 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ደቡብ ወሎና ትግራይ ምዕራባዊ ዞኖች ለ385 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጠ
ደሴ/ ሲቲት ሁመራ/ መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) በአማራ ደቡብ ወሎና ትግራይ ምዕራባዊ ዞኖች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማርት ጥያቄ ላቀረቡ 385 ባለሃብቶች ፈቃድ መሰጠቱ ተገለጸ።
የደቡብ ወሎ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ዘቢባ አሊ ለኢዜአ እንዳሉት በአካባቢው ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመጠቀም ጥያቄ ላቀረቡ 321 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ፈቃድ የተሰጣቸው እነዚህ ባለሀብቶች ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ መሆኑን አመልክተዋል።
በሆቴልና ቱሪዝም ፣ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ ፣ በግብርናና ሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ የወሰዱት ባለሀብቶቹ ከ7 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎችም የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል ብለዋል።
ከመካከላቸውም 33 ባለሃብቶች የተሰጣቸው 45 ሄክታር በላይ መሬት በመጠቀም ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ያመለከቱት ኃላፊዋ ቀሪዎቹ ስራ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዞኑ ያለው የተረጋጋ ሰላም፤ አየር መንገድ፤ ባቡር ጣቢያ፤ የከርሰ ምድር ውሃ፤ ኢንዱስትሪ ፓርክ፤ ደረቅ ወደብና ሌሎችም ምቹ ሁኔታዎች ኢንቨስትምንቱን እያነቃቁት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው ወሎ ለኢንቨስትመንትና ቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ በርካታ ታሪካዊ፤ ኃይማታዊና ባህላዊ ቦታዎች ቢኖሩትም በሚፈለገው ልክ ለምቶ ጥቅም እየሰጠ አይደለም ብለዋል።
ለዚህም የመስህብ ሃብቶችን ትኩረት ሰጠቶ ካለማስተዋወቅ ጀምሮ በቅንጅት መጓደል፤ በመሰረተ ልማት ተደራሽ አለመሆን ባለሃብቱን በመሳብ አካባቢው እንዲለማ አለመደረጉን ጠቅሰዋል ፡፡
አሁን ላይ ችግሮችን ገምግሞ በማስተካከል ባለሃብቶች ወደ አካባቢው መጥተው ያለምንም ችግር ወደ ልማት እንዲገቡ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን አብራርተዋል ።
በኮምቦልቻ ከተማ ባለ ኮከብ ሆቴል ለመገንባት 21 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ መቀበላቸውን የተናገሩት ደግሞ የአይቸሽ ተስፋዬ ሪዞርትና ሆቴል ተወካይ አቶ ገበየሁ ታደሰ ናቸው፡፡
ቦታውን ለማግኘት በርካታ ውጣ ውረድ ማሳለፋቸውን ጠቁመው፤አሁን ላይ በ20 ሚሊዮን ብር ወደ ግንባታ መግባታቸውን ጠቁመዋል።
ግንባታውንም በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት ይገባል ብለዋል።
በኮምቦልቻ ከተማ በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክበው ወደ ስራ መግባታቸውን የገለፁት ደግሞ የ"ያለው ይልማ" ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ውድነህ መኮንን ናቸው።
በዞኑ በተያዘው የበጀት ዓመትም ለ313 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዷል።
በሌላ በኩል በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በ2012 በጀት ዓመት ከሁለት ቢሊዮን 200 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 64 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን የዞኑ የኢንቨስትመንትና ኤክስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኃይሉ ገብረእግዚአብሔር ገልጸዋል።
ባለሀብቶቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ ከ7ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።
የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከወሰዱት ውስጥ 24 ባለሃብቶች በማኑፋክቸሪንግ ቀሪዎቹ በእርሻ፣ ሆቴል፣ ቱሪዝም፣ ጤናና ማዕድን ማምረት ዘርፎች ለመሰማራት እንደሆነ አመልክተዋል።
በርካታ ባለሃብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ባሳዩት ፍላጎት በበጀት ዓመቱ የተያዘው እቅድ ማሳካት መቻሉን ኃላፊው አመልክተው ወደ ማምረት የገቡ ባለሀብቶች እንዳሉም አስረድተዋል።
የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከወሰዱ ባለሀብቶች መካከል የሃበሻ ፉድ ኮምፕሌክስ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዘነበ ኪዳነማርያም አንዱ ናቸው።
በዳንሻ ከተማ 30 ሚሊዮን ብር በሆነ ካፒታል የዳቦ ዱቄት የፋብሪካው መገንባታቸውን የገለጹት አቶ ዘነበ ፋብሪካው በቀን 820 ኩንታል የዳቦ ዱቄት በማምረት ለአከባቢው ማህበረሰብ ለማከፋፈል እንደተቋቋመ ተናግረዋል።
ለፋብሪካው የሚያስፈልግ የትራንስፎርመርና ማሽን ስራ መጠናቀቁን ጠቅሰው፤ ቀሪ ስራ ለማከናወን 10 ሚሊዮን ብር ከባንክ ብድር ጠይቀው ምላሹን እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፋብሪካው ለ50 ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።
በሰቲት ሁመራ ከተማ በ10 ሚሊዮን ብር ካፒታል የግል የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በማስገነባት ላይ የሚገኙት የግንባታ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኒኤል ገብረትንሳኤ በበኩላቸው የሆስፒታሉ ግንባታ 60 በመቶ መድረሱንና ዘንድሮ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ገልጸዋል።
ባለሀብቶቹ የልማት ባንክ ለኢንቨስትመንት ስራዎች የሚያደርገው የገንዘብ ብድር ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትየጵያ ልማት ባንክ የሁመራ ቅርንጫፍ የስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ደረጀ አማኒኤል በበኩላቸው ባንኩ እስካሁን በእርሻ ኢንቨስትመንት ለተሰማሩ 25 ፕሮጀክቶች 20 ሚሊዮን ብር ብድርና 50 ሚሊዮን ብር ደግሞ የብድር ክፍያ ማራዘሙን ገልጸዋል።
ባንኩ በዋናነት የፕሮጀክት ብድር፣ስራ ማስኬጃና ለማሽን ግዥ ላይ ትኩረት አድረጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጾ ከዚህ ውጭ ያሉ የብድር አገልግሎቶች ለጊዜው መቆሙን አስረድተዋል።