በጌዴኦ ዞን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ስኳርና ዘይት በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በጌዴኦ ዞን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ስኳርና ዘይት በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተያዘ
ዲላ ግንቦት 4/2010 ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ስኳርና ዘይት በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን የጌዴኦ ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው ምክትልና የንግድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጋሹ ለኢዜአ እንደገለጹት የስኳርና ዘይት ህገ-ወጥ የንግድ እንቅሰቃሴን ለመከላከል በተቋቋመ ኮሚቴና በህዝብ ተሳትፎ እየሰራ ነው። በዞኑ ህገ-ወጥ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ የሚታይ በመሆኑ ከመምሪያው፣ ከፀጥታና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ዝውውሩን ለመከላከል ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል ። "በግብረ-ኃይሉ ክትትልና በህብረተሰቡ ጥቆማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 639 ኩንታል ስኳርና 3ሺህ 900 ሊትር ዘይት በተለያዩ ግለሰቦች ሲዘዋወር ተይዟል" ብለዋል ፡፡ "በ2008 ዓ.ም በወጣ አዋጅ ስኳር፣ ዘይትና መሰል መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ግለሰቦች ያለመንግስት ፈቃድ እንዳያዘዋውሩና እንዳያከፋፍሉ ተደንግጓል" ያሉት አቶ ወርቅነህ፣ ይህን በመከላከል የተያዘውን ስኳርና ዘይት ፍቃድ ባላቸው ንግድ ቤቶች አማካይነት ለህብረተሰቡ እንዲደርስ መደረጉን አስረድተዋል ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ ቅቤ፣ ማርና የበቆሎ ዱቄት ለተጠቃሚዎች ከመቅረባቸው በፊት መያዛቸውን ገልጸዋል። "78 አይነት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የታሸጉ ምግቦች፣ መጠጦችና ሌሎች ምርቶችም በክትትል ተይዘው እንዲወገዱ ተደርጓል" ብለዋል ፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ ከህገ-ወጥ ንግድና ዝውውር ጋር በተያያዘ በህግ ቁጥጥር ሥር የዋሉ 20 ግለሰቦች ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ነው ። በጌዴኦ ዞን ፖሊስ መምሪያ የኢንዶክትሪኔሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና ሥራ ሂደት ኃላፊ ኮማንደር አሸናፊ ሆጤሳ በበኩላቸው አካባቢው ከፍተኛ ህገ-ወጥ ንግድ እንቅስቃሴ የሚታይበት መሆኑን አመልክተዋል። የቁጥጥር ሥራው የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት ያለበት በመሆኑ በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ "በቀጣይ ቁጥጥሩን ለማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ለመስራት አቅጣጫ መያዙን ነው" የገለጹት ። ባለፉት ዘጠኝ ወራት የፍጆታና ሌሎች እቃዎች ሊያዙ የቻሉት በአብዛኛው በሕብረተሰቡ ጥቆማ መሆኑን የገለፁት ኮማንደር አሸናፊ "ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የማሕበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ሥራ ላይ አተኩረን እንሠራልን" ብለዋል ፡፡