በህገወጥ መንገድ ገንዘብ ያከማቹ ሰዎች ከፍተኛ የንብረት ግዥና የውጭ ምንዛሬ ሊፈፅሙ ስለሚችሉ የተጠናከረ ቁጥጥር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
በህገወጥ መንገድ ገንዘብ ያከማቹ ሰዎች ከፍተኛ የንብረት ግዥና የውጭ ምንዛሬ ሊፈፅሙ ስለሚችሉ የተጠናከረ ቁጥጥር ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ያከማቹ ሰዎች ከፍተኛ የንብረት ግዥና የውጭ ምንዛሪ ሊፈጽሙ ስለሚችሉ የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።
ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 ብር ኖት መቀየሯን እንዲሁም አዲስ ባለ 200 ብር ኖት ወደ ሥራ ማስገቧቷን ይፋ ማድረጓ ይታወቃል።
የገንዘብ ኖት መቀየሩን ተከትሎ በሕገወጥ መንገድ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የያዙ ግለሰቦች ንብረት ሊገዙና የውጭ ምንዛሪ ሊፈጽሙ ስለሚችሉ በዝውውር ሂደቱ ላይ መንግሥት የተጠናከረ ቁጥጥር እንዲያደርግ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ምሁር አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ መዚድ ናስር የገንዘብ ኖት መቀየሩ ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ የሚዘዋወረውን ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ ሙስናንና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቀልበስ፣ የገንዘብ እጥረትን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የገንዘብ ኖት መቀየር ከባንክ ውጭ የሚገኝን ገንዘብ ወደ ሥርዓት ለማስገባትና ገበያውን ለማረጋጋት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለውም ተናግረዋል።
የገንዘብ ኖቱን ወደ መቀየር ሲገባ ብዙ ገንዘብ በእጃቸው የያዙ ሰዎች ብሩን ወደ ውጭ ገንዘቦች ሊመነዝሩት፣ ንብረት ሊገዙበት እንደሚችሉ የጠቆሙት አቶ መዚድ፤ ''ይህ ደግሞ የገንዘብ ኖት የመቀየሩ ዓላማ እንዳይሳካ በማድረግ የውጭ ምንዛሪውን ምጣኔ ሊያንረው ይችላል'' ብለዋል።
በመሆኑም በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ያከማቹ ሰዎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ የሚያስከትል ድርጊት እንዳይፈጽሙ ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የገንዘብ ኖት መቀየሩ የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ቁጥጥር ፖሊሲ ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያስችል ገልጸው፤ ቁጠባንና የባንኮችን ተቀማጭ ሂሳብ ለማሳደግ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ለማስፋት እንደሚረዳ አቶ መዚድ ተናግረዋል።
ባንኮችና የግብር ሰብሳቢ ተቋማት አብረው የሚሰሩበት ሥርዓት ከተዘረጋ ሙስናና የታክስ ስወራን ሊያስቀር እንደሚችል ጠቅሰዋል።
የገንዘብ ኖት መቀየር ከኑሮ ውድነት መባባስና ከውጭ ምንዛሪ ከፍ ማለት ጋር የተያያዘ አለመሆን በገንዘብ መቀየር ሂደቱ ሊያጋጥም የሚችልን ችግር እንደሚቀንስም ገልጸዋል።