ቀጥታ፡

አዲስ የገንዘብ ኖት መጠቀም የተስተካከለ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ያደርጋል --የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) አዲስ የገንዘብ ኖት መጠቀም የተስተካከለ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ነባሮቹን ባለ10፣ 50 እና 100 ብር የገንዘብ ኖቶችን በሌላ በመቀየርና አዲስ የ200 ብር ኖት በማካተት ለግብይት መጠቀም እንደምትጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፀሐፊ አቶ የሱፍ አደምኑር እንደሚሉት አዲስ የገንዘብ ኖት ተዘጋጅቶ ወደ ገበያ ማስገባት ሕገወጥ ነጋዴዎችን ለመከላከል ከማስቻሉ ባለፈ ሕጋዊ ሥርዓት ተከትለው ለሚሰሩ ነጋዴዎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

"ያለአግባብ በግለሰቦች እጅ ተከማችቶ የሚገኝ ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲገባ ስለሚያደርግ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በሚከናወኑ ተግባራት የራሱን ሚና ይጫወታል" ሲሉም አመልክተዋል።

በገበያ ሥርዓት ላይ ሀሰተኛ የብር ኖቶች እንዳይሰራጩና የተዛባ የንግድ ሥርዓትን ለመከላከል እንደሚጠቅምም አመልክተዋል።

መንግሥት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመታደግ የወሰደው እርምጃ ተገቢ መሆኑንም አቶ የሱፍ ተናግረዋል።

አቶ የሱፍ እንዳሉት ነጋዴው ማኅበረሰብ መንግሥት የጀመረው የዕድገት ጉዞ ከግብ እንዲደርስ የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል።

የንግድ ሥርዓቱ በተዛባ ሁኔታ እንዳይቀጥል ነጋዴው ሕጋዊ ሥርዓትን ተከትሎ መሥራትና በእጁ ላይ ያለውን ገንዘብ ፈጥኖ መለወጥ እንዳለበት መክረዋል።

መንግሥትም አስፈላጊውን ቁጥጥርና ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባም አቶ የሱፍ አስገንዝበዋል።

ይፋ የተደረጉት አዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች ለአገልግሎት ሲበቁ ለሕገወጥ እንቅስቃሴዎች የሚደረግን ድጋፍ፣ ሙስናንና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቆጣጠር ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መጠቆማቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም የገንዘብ ኖቶቹ እንዲኖራቸው የተደረገው የደህንነት ገፅታዎች ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በማመሳሰል ለማተም የሚደረጉ ሕገወጥ ጥረቶችን ለማስቀረት እንደሚያግዙም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም