በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ5 ሰዎች ሕይወት በመብረቅ እና በትራፊክ አደጋ አለፈ

71

አሶሳ፣ መስከረም 5/2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ወረዳ በረዶ ቀላቅሎ ከጣለ ኃይለኛ ዝናብ ጋር የወረደ መብረቅ የአራት ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱን ፖሊስ አስታወቀ።
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ራማ ሰይድ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ትናንት ማምሻውን በወረዳው አምባ 17 እና አምባ ዘጠኝ ቀበሌ ከሃይለኛ ዝናብ ጋር የወረደ መብረቅ አደጋ አስከትሏል።

በአደጋው አንድ የ12 ዓመት ህጻንን ጨምሮ የአራት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን አዛዡ ገልጸዋል።

“በአደጋው ወቅት ሟቾቹ ሲያከናውኑት የነበረውን የእርሻ ስራ አቁመው በአካባቢው በሚገኝ አነስተኛ ጎጆ ቤት ተጠልለው ነበር” ብለዋል።

ከዚህ ሌላ በዝናቡ በቀበሌው በ50 ሄክታር ላይ የሚገኝ በቆሎ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር እና ጤፍ ሰብል መውደሙን አዛዡ አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ከዞኑ ሆሞሻ ከተማ ወደ ቱንጋ አሩሜላ ከተማ በሞተር ብስክሌት ሲጓዝ የነበረ አንድ ግለሰብ ከመንገድ ዳር ከሚገኝ ምልክት ጋር በመጋጨቱ ህይወቱ ማለፉን የሆሞሻ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር አብዱልመጅድ ኑረዲን ገልጸዋል፡፡

የአደጋው ምክንያት ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር መሆኑንም አዛዡ አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት እየጣለ ከሚገኘው ሃይለኛ ዝናብ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም ከሚችል ጉዳት እንዲሁም ከትራፊክ አደጋ እራሱን እንዲጠብቅ የፖሊስ አዛዦቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም