ለችግር የተጋለጡ አረጋዊያንን ለመደገፍ መገናኛ ብዙሃንና የፍትህ አካላት ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

105

አዳማ፣ መስከረም 05/2013 ( ኢዜአ) በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለችግር የተጋለጡ አረጋዊያን ለመደገፍ መገናኛ ብዙሃን ተቋማትና የፍትህ አካላት በሙያቸው ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በአረጋዊያን ላይ የሚደርሱ አድሎ፣ ማግለልና ተያያዥ ችግሮችን ለማቃለል የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና የፍትህ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማመቻቸት ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ቶማስ ኩዬ እንደተናገሩት መድረኩ የተዘጋጀው በየዓመቱ የሚከበሩ የአረጋዊያን ቀን አስመልክቶ ሊሰሩ በታቀዱ ተግባራት ላይ የባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለማሳደግ ነው።

አረጋዊያን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ መሆናቸውን አመልክተው፤ በተለይም በሚደርስባቸው አድሎና ማግለል ሀብት ንብረታቸውን ጭምር በወዳጅ ዘመዶቻቸው እየተቀሙ ጎዳና ላይ ወድቀው ለልመና እየተዳረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ይህን ችግር ለማቃለል በየደረጃው የሚገኙ የፍትህ አካላትና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሚናቸው የጎላ በመሆኑ  በሙያቸው  አጋዥ  ሊሆኑ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የህብረተሰቡን  የአስተሳሰብና የአመለካከት ችግር ለመፍታት ከሚከናወነው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በተጨማሪ የፍትህ አካላት መብታቸው እንዲከበር ማገዝና መደገፍ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

በዚህም ከፍትህ ስርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ መብታቸው እንዲከበር፣ በልማቱ እንዲካተቱ፣ ተሳታፊና የአገልግሎቱ ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻል እንችላለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ከሚገኙ 7 ሚሊዮን አረጋዊያን  ውስጥ  ከ1 ሚሊዮን 200  በላይ የሚሆኑት የሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በሚኒስቴሩ የማህበራዊ ደህንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ጀምበር ናቸው።

ፕሮግራሙ በሀገሪቱ 386 ወረዳዎችና  ዋና ዋና ከተሞች የሚካሄድ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም አረጋዊያኑ ባላቸው እውቀት፣ አቅምና ልምድ የስራ እድል እንዲያገኙ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ማስፋት ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በአዳማ ከተማ ለሶሰት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረኩ  ከግልና ከመንግስት የመገናኛ ብዙሃን  እንዲሁም ከፍትህ ተቋማት የተውጣጡ ሙያተኞችና የስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም