ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደ ግብጽና ሱዳን የሚሄደውን የውሃ ፍሰት አይቀንሰውም - ፕሮፌሰር አሾክ ስዌይን

\

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5/2012 ( ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግብፅና ሱዳን የውሃ ፍሰትን በመቀነስ ጉዳት እንደማያደርስባቸው በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/አንድ ባለሥልጣን ገለጹ።

የድርጅቱ ዓለም አቀፍ የውሃ ትብብር ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር አሾክ ስዌይን ለፍራንስ 24 ቴሌቪዥን ጣቢያ እንዳመለከቱት ግድቡ ከኃይል ማመንጫነት ያለፈ ሚና ስለሌለው በሁለቱ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት አያደርስም።

እንዲያውም ግድቡ አገሮቹን ጎርፍ ከሚያደርስባቸው ጉዳት ለመከላከል እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል።

ግድቡ ወደ አገሮቻቸውን የሚገባውን የውሃ መጠን ይቀንስብናል በሚል ስጋት ከኢትዮጵያ ጋር  ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት እያካሄዱት ባለው ድርድር መተማመን እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል ብለዋል።

ፕሮፌሰር  ስዌይን እንደሚሉት የኃይል ማመንጫ ግድቦች አገልግሎት ሲሰጡ የውሃ ፍሰት የመቀነስ ስጋት ሊያድር አይገባም።  

ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ የመስኖ ወይም ሌላ ዓላማ ያለው ግድብ ባለመሆኑ በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት ታደርሳለች የሚል ስጋት ተገቢ እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ 85 በመቶ ድርሻ ያላት ቢሆንም፤ በአግባቡ አልተጠቀመችበትም የሚሉት ሊቀመንበሩ፣ ግብፅና ሱዳን ግን ወንዙን ተጠቅመው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መገንባታቸውን ጠቁመዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት መሆኑንና ግንባታው ሲጠናቀቅ  ለአገሪቱ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስታውቀዋል።

ግድቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የጋራ ተጠቃሚነቷን ታረጋግጥበታለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን እያደረጉት ያለው ድርድር በቅርቡ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚል እምነት እንዳልነበራቸው የሚገልጹት ፕሮፌሰር ስዌይን፤ በሱዳንና ግብፅ  እየተከሰተ ያለው ጎርፍ ሃሳባቸውን ሊያስቀይራቸው እንደሚችል ተናግረዋል።

"ሱዳን በጎርፍ እየተጠቃች ነው፤ ግብፅም በተመሳሳይ በመሆኑም ግድቡ በሁለቱ አገሮች የሚከሰተውን ጎርፍ በመከላከል ሊያግዛቸው ይችላል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሁለት ወራት  በፊት ግድቡን  ለመጀመሪያ ዙር 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ መሙላቷ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየጣለ ባለው ዝናብ የውሃ አካላት በመሙላታቸው ጉዳት እያስከተሉ  ነው።

በሱዳን እየተከሰተ ባለው ጎርፍ ከ100 በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡ጎርፍ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በደረሰው መጥለቅለቅም የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ መታወጁን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የምትገነባው ግድብ ሁለቱን አገሮች እንደማይጎዳ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።ጉዳቱ ከሚቀንሱ ተግባራት አንዱ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች የሚከሰተውን ጎርፍ መቀነስ እንደሆነ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም