የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በልደታ ክፍለ ከተማ በነበረው የአንድ ወር ቆይታ 71 ሚሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በልደታ ክፍለ ከተማ በነበረው የአንድ ወር ቆይታ 71 ሚሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5/2012 ( ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ በነበረው የአንድ ወር ቆይታ 71 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ።
በገቢ ማሰባሰብ መርሃ ግብሩ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል መገባቱንም የክፍለ ከተማው ስራ አስፈፃሚ ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በተለያዩ የአገሪቱ ከፍሎች እየተዘዋወረ አንዱ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገድ ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል።
ዋንጫው ላለፈው አንድ ወር በልደታ ክፍለ ከተማ በነበረው ቆይታ በቦንድ ግዥና በስጦታ 71 ሚሊዮን ብር ሲሰበሰብ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል መገባቱን የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታረቀኝ ገመቹ ገልጸዋል።
በክፍለ ከተማው 70 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ከእቅድ በላይ መሳካቱን ተናግረዋል።
ለዚህም የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮችን በመፍጠርና የማህበረሰቡም ተሳትፎ ጠንካራ ስለነበር ከታሰበው በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
አራዳ ክፍለ ከተማ በዛሬው እለት ዋንጫውን ከልደታ ክፍለ ከተማ የተረከበ ሲሆን በቀጣዮ አንድ ወር ገቢ እንደሚያሰባስብ ይጠበቃል።
በመርሃ ግበሩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመዲናዋ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በግድቡ ዙሪያ የህዝቡ ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2012 ዓ.ም በግንባታው ዙሪያ የነበረው ክንውን እና በዲፕሎማሲው መስክ የታየው ስኬትም እንዲሁ።
በመሆኑም በ2013 ዓ.ም የግድቡን ግንባታ ወሳኝ ምዕራፍ ለማድረስ የመንግስት ዝግጁነት እንዳለ ሆኖ የህዝቡም ተሳትፎ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በነሃሴ 2012 ዓ.ም ብቻ ለግድቡ ግንባታ ከሌሎች ወራቶች የላቀ ከፍተኛ ገንዘብ ተሰብስቧል።
በነሃሴ ወር በቦንድ ሽያጭና በስጦታ እንዲሁም በ8100 የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ታውቋል።