በወረዳ ላሉ የብልጽግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች ስልጠና መስጠት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በወረዳ ላሉ የብልጽግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች ስልጠና መስጠት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5/2012 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ በወረዳ ላሉ የፓርቲው መካከለኛ አመራሮች ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ስልጠና መስጠት ጀመረ።
ስልጠናው የፓርቲና የመንግስት አመራር አቅምን በመገንባት በከተማ እና በአገር ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማፋጠን ያለመ መሆኑም ተመልክቷል።
የኢዜአ ሪፖርተሮች በአዲስ አበባ አራዳና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በወረዳ ደረጃ ላሉ መካከለኛ አመራሮች መሰጠት የተጀመሩ ስልጠናዎችን ተዘዋውረው ቃኝተዋል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት መስጠት በተጀመረው ስልጠና ከወረዳዎች የተውጣጡ 290 የብልጽግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የአራዳ ክፍለ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንዳሉት ስልጠናው አመራሩ የተግባርና የአመለካከት አንድነት እንዲይዝ የሚያስችል ነው።
ስልጠናው የፓርቲና የመንግስት አመራር አቅምን በተሻለ በመገንባት በከተማ እና በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማፋጠን ያለመ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ አመራሩ የብልጽግና ፓርቲን ራዕይ፣ መንገድና መሰረታዊውን በአግባቡ እንዲያውቅ ለማስቻል ታስቦ እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት።
በአብሮነትና በአንድነት መንፈስ የህዝቦችን ተሳትፎ በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚችል አመራር ለመፍጠር አጋዥ እንደሆነም አስረድተዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ከዛሬ ጀምሮ መሰጠት የተጀመረው ስልጠና ለውጡን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶችን የሚሻገርና ብቁ አመራር ለመፍጠር ያግዛል።
'' አመራሩ ለቀጣይ ተልዕኮ ስኬታማነት አቅም እንዲይዝ በማድረግ በኩልም ጠቀሜታው የጎላ ነው'' ብለዋል።
በተመሳሳይ ዜና ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮችም ስልጠናው " ወቅታዊ ሁኔታዎችን መሻገሪያ ትልሞች " በሚል መሪ ቃል መሰጠት ተጀምሯል።
በስልጠናውም በክፍለ ከተማው ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ 325 መካከለኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የክፍለ ከተማው የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አበራ መካከለኛ አመራሩ ለህዝብ ቅርብ መሆኑን ገልጸው፤ ስልጠናው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ብዥታዎችን ማጥራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም አመራሩ በፓርቲው አጠቃላይ አቅጣጫዎች ላይ ግልጽ ግንዛቤ ኖሮት ወደ ስራው እንዲመለስ የሚያግዝ ስልጠና መሆኑን ነው የተናገሩት።
"መካከለኛ አመራሩ ብዙ መስራት የሚችልና ለህዝብ ቅርብ እንደመሆኑ የራሱን ኃላፊነት እንዲወስድ የሚያግዝ ስልጠና ነው" ብለዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች አቶ እስማኤል አብዱ እና አቶ አብራራው እሸቴ በበኩላቸው ስልጠናው በህዝብና በአመራሩ መካከል ያለውን ግንኙነት በግልጽነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
አመራሩን ከአገልግሎት ሻጭነት ወደ አገልግሎት ሰጭነት እንዲሸጋገር በማድረግ በኩልም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት።
የአመራሩን አቅም በመገንባት ከውሸት ሪፖርት ይልቅ በተጨባጭና በተግባር የሚታይ ሥራ ለመስራት የሚያግዘው መሆኑንም ተናግረዋል።
ስልጠናው በጽሁፍና በቪዲዮ በተዘጋጁ ሰነዶች ላይ ተመስርቶ እየተሰጠ መሆኑም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ በወረዳ ደረጃ ላሉ የፓርቲው መካከለኛ አመራሮች ለአምስት ተከታታይ ቀናት እየሰጠ ያለው ስልጠና በሌሎች ክፍለ ከተሞችም ዛሬ መሰጠት መጀመሩ ለማወቅ ተችሏል።