የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ያስችላል የተባለው ባጅ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ያስችላል የተባለው ባጅ
አዲስ አበባ መስከረም 5/2013 (ኢዜአ) በአለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ወይም መድሃኒት ለማግኘት በፍጥነት እየሰሩ ቢሆንም፤ በርካታ ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶች በኦን ላይንና በተለያዩ ሚዲያዎች እየተዋወቁ ይገኛል።
በናይጄሪያ፣ሱዳን እና ከአፍሪካ ውጭ ባሉ ሌሎች አገራት ፓለቲከኞች ‘ቫይረስ ተከላካይ’ ፣ ‘ቫይረስ መካች’ እና የተለያዩ ስያሜዎች የተሰጠው ባጅ አድርገው መታየታቸውንና ባጆቹ በአለም አቀፍ ደረጃ ለሽያጭ መዋላቸውን ቢ ቢ ሲ ዘግቧል።
በአብዛኛው በጃፓንና በሆንግ ኮንግ ተመርቶ ወደ ተለያዩ አገራት የሚገባ መሆኑም ነው የተገለጸው።
እነዚህ ባጆች ከወረቀት የሚሰሩ ሲሆን በልብሶች ላይ እንደ መታወቂያ ካርዶች ሊንጠለጡ እንደሚችሉም ተጠቅሷል።
ባጆቹ ኬሚካል በመርጨት የኮሮና ቫይረስን ጨምሮ ሌሎች ቫይረሶችንና ባክቴሪያዎችን ይገላሉ ቢባሉም ፤ ኤክስፐርቶች ግን ጉዳት ሊያሰከትሉ ይችላሉ እንጂ ሊሰሩ አይችሉም ማለታቸውም ተጠቁሟል።
ኤክስፐርቶች ባጁ የኮቪድ 19 መድሃኒት ለማግኘት ከተጨነቁ ሰዎች ጥቅም ለማግኘት የተሰራ ማጭበርያ ነው ማለታቸው ተገልጿል፤ ከዚህም ባለፈ ሰዎች ላይ አለርጂክ ሊፈጥር ይችላል ብለዋል።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኬርና ሌሎች የአገሪቱ ባለስልጣናት ፣አንድ ናይጄሪያዊ ሴናተር ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት፣ በዛምቢያ የአንድ አየር መንገድ ሰራተኞች፣የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባዩን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት ባጁን አድርገው ከታዩት መካከል ይጠቀሳሉ።
ሆኖም አብዛኛዎቹ እነዚህ ባለስልጣናት በኮቪድ 19 በሽታ መያዛቸው ተጠቁሟል።
የዛምቢያ የአንድ አየር መንገድ በበኩሉ ሰራተኞች ባጁን ማድረጋቸው እንደሚቀጥሉ ያስታወቀ ቢሆንም ሰራተኞቹ ባጁን አድርገው የሚያሳየው ፎቶ ከማህበራዊ ሚዲያ ገጽ መነሳቱ በዘገባው ተመልክቷል።