የፀረ ሙስናው ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የፀረ ሙስናው ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ
አዳማ ፣መስከረም 04/2013 (ኢዜአ) የፀረ ሙስናው ትግል ህብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ በቀጣይ አስር ዓመታት መሪ እቅድ ዙሪያ በየደረጃው ያሉ ፈፃሚዎች ግልጽ ግንዛቤና ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀመሯል።
በስልጠናው መድረክ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ እንደተናገሩት የጸረ ሙስናን ትግል ተግባር ተኮር አስተምህሮ በማከናወን ህብረተሰቡን የማንቃትና በባለቤትነት የማሳተፍ ስራ በስፋት ይከናወናል።
በዚህም በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የፀረ ሙስና ትግሉን እናስቀጣጥላለን ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በተለይም ተሿሚዎች፣ የህዝብ ተመራጮችና ሰራተኞች ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ይደረጋል ብለዋል።
በፈፃሚው ዘንድ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖርና እቅዱን በእውቀት መፈፀም እንዲችሉም ክህሎትና አቅማቸውን የማዳበር ስራ ከወዲሁ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
እስካሁን የተሰራው የፀረ ሙስና ትግል ውጤት ህዝቡ ከሚጠብቀው በታች መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኮሚሽኑ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሻኒቦ ናቸው።
በቀጣይ በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣትና የህዝቡን ፍላጎት ያማከለ ተግባር ለማከናወን በአዲስ አሰራርና አደረጃጀት ወደተግባር ገብተናል ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ በሀገሪቱ በፀረ ሙስና ትግል በተከናወኑ ስራዎች ኢትዮጵያ ከነበረችበት አንድ መቶ ሃያ ስድስተኛ ደረጃ ወደ ዘጠና ስድስተኛ ማሻሻሏን ጠቅሰው፤ ውጤቱ የመጣው የለውጡ ኃይል ባሳየው ቁርጠኝነት መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ አስር ዓመታት በፀረ ሙስና ትግል ከአፍሪካ ቀዳሚ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሩዋንዳ፣ ቦትስዋናና ሲልሺየስ ተርታ ለማሰለፍ ከወዲሁ ወደ ተግባር ገብተናል ብለዋል።
በአዳማ የተዘጋጀው ስልጠና ኮሚሽኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ኃይሉ በእቅዱ ላይ ግልጽ ግንዛቤና ክህሎት አግኝቶ ለተፈፃሚነቱ እንዲረባረብ ለማስቻል እንደሆነም አስረድተዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት በግልና መንግስት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ስነ ምግባር ግንባታ፣ የሃብት ምዝገባና ህዝባዊ ንቅናቄ ቀዳሚ ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
የኮሚሽኑ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አዲስ ለማ የፀረ ሙስና ትግሉን ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ የአለም አቀፍ ቋንቋ በመጠቀም መረጃዎችን ለትራንስፓራንስ ኢንተርናሽናል ተቋም ተደራሽ እናደርጋለን ብለዋል።
በዚህም የሀገሪቷን የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ ደረጃ ለማውጣት ትክክለኛ መረጃዎች ተደራሽ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
እቅዱን ውጤታማ ለማድረግም ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር አብረን እንሰራለን ብለዋል።
በአዳማ ከተማ ዛሬ የተጀመረውና ለሁለት ቀናት በሚቆየው ስልጠና በኮሚሽኑ አዲሱ አሰራርና አደረጃጀት ላይ ጭምር ፈጻሚዎች ግንዛቤና ክህሎት እንዲኖራቸው እንደሚደረግ ተመልክቷል።