ቀጥታ፡

ከሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ 1 ሺህ 440 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመመለሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4/2013(ኢዜአ) በያዝነው ወር በሳዑዲ ዓረቢያ ከምትገኘው ጅዳ ከተማ 1 ሺህ 440 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፊታችን ሐሙስ ከሊባኖስ 132 ኢትዮጵያውያን ይመጣሉ።

የሚኒስቴሩ የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል መስፍን ገብረማርያም ከመስከረም 6 እስከ 26/2013  ባለው ጊዜ  ዜጎችን ከጄዳ ለመመለስ ዝግጅት መጠናቀቁን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚህም የፊታችን ረቡዕ 300 ዜጎች ወደ አገራቸው ይመለሳሉ ብለዋል።

በቀጣይም  ቀሪዎቹ  ስደተኞች  እንደሚመለሱ  አቶ መስፍን አስታውቀዋል።

ተመላሾቹ በሕገ ወጥ መንገድ በቀይ ባህር በኩል ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የገቡና በእስር ቤትና በሕገ ወጥ ስደተኞች ማቆያዎች ውስጥ እንደነበሩ አመልክተዋል።

ዜጎቹን ወደ አገራቸው የሚመለሱት በሚኒስቴሩ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣በጅዳ የኢትዮጵያ     

ቆንስላ ጽህፈት ቤት፣የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ተቋም(አይ ኦ ኤም)ጋር በመተባበር እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ባለፈው ሳምንት በሳዑዲ ዓረቢያዋ ሪያድ ከተማ ይኖሩ የነበሩ 147 ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አቶ መስፍን አውስተዋል።

በቀጣይም በሪያድ የሚገኙ 334 ዜጎችን ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ዳይሬክተር ጄኔራሉ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ሐምሌ ወር 2012 በሊባኖስ መዲና በቤይሩት ወደብ በደረሰው ፍንዳታ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ 132 ኢትዮጵያውያን የፊታችን ሐሙስ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ዜጎቹ በደረሰባቸው ችግር በመጠለያ ውስጥ የሚገኙና የቲኬት ወጪያቸውም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች እንደተሸፈነም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም