ቀጥታ፡

በዱብቲ ወረዳ የሞባይል ስልክ ኔትወርክ ሶላር ባትሪዎችን ዘርፈዋል የተባሉ ሶስት ተጠርጣሪዎች ተያዙ

ሰመራ፣ መስከረም 4/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ ለሞባይል ስልክ ኔትወርክ የሚያገለግል ሶላር ባትሪዎችን ሰርቀው ለመሰወር ሲሞክሩ ደረስኩባቸው ያላቸውን ሶስት ተጠርጣሪ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ዘይኑ አሊ እንደገለጹት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ጳጉሜን 5/2012 ዓ.ም ማታ ሶስት ሰዓት አካበቢ ባትሪዎቹን በወረዳው ሰርዶ ቀበሌ ልዩ ስሙ ፋናል ከተባለ ቦታ በመስረቅ በተሽከርካሪ ጭነው ለመሰወር ሲሞክሩ በህብረተሰቡ ጥቆማ ነው።

ለሞባይል ስልክ አገልገሎት የሚውሉትን በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ  ባትሪዎችን  ሰርቀው ለመሰወር ሲሞክሩ ደርሸባቸዋል ያላቸው እነዚህ ግለሰቦች በታርጋ ቁጥሩ  ኮድ3- 27926 አዲስ አበባ በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሸከርካሪ እንደጫኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ወደ መሃል ሀገር ለመውሰድ በተሽከርካሪው ላይ ጭነዋቸው የነበሩ አስር በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የሞባይል ስልክ ኔትወርክ ባትሪዎች እንደተገኘባቸው አስረድተዋል።

በክልሉም ሆነ ወረዳው የቴሌና መሰል መሰረተ-ልማቶች በህብረተሰቡ ተሳትፎ ጥበቃ  ስለሚደረግ ከአሁን ቀደም  እንደዚህ ዓይነት ወንጀል አጋጥሞ እንደማያውቅ  ተናግረዋል።

የሀገርና ህዝብን ጥቅም ወደጎን በመተው በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚጥሩ ግለሰቦችን ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ስርዓት ለማስያዝ የጸጥታው መዋቅር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም