የኢትዮጵያ መንግሥት አዳዲስ የብር ኖቶችን ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግሥት አዳዲስ የብር ኖቶችን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 04/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግሥት አዳዲስ የደህንነት ገጽታዎች እና ሌሎች መለያዎች የተካተቱባቸው የገንዘብ ዓይነቶችን ለግብይት ሊያውል ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ይፋ እንዳደረገው ነባሮቹ የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ዓይነቶች ሙሉ ለሙሉ የሚተኩ ይሆናል።
የ5 ብር ገንዘብ ባለበት ቀጥሎ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ወደ ሣንቲም እንደሚቀየር ተገልጿል።
ይህ የገንዘብ ቅያሪ መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ የሚዘዋወረውን ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ ሙስናንና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቀልበስ ያለመ ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ እጥረትን ለመቋቋም እንዲችሉ ያግዛል ተብሎለታል።
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የሕትመት ሥራ ተገባዶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግምጃ ቤት እንደሚገኝ ታውቋል።
የስርጭት ስርዓት እና ዕቅድ የተዘጋጀ ሲሆን በሚመለከታቸው አካላት አማካኝነት የሚተገበር ይሆናል ተብሏል።
በገንዘብ ቅያሬው ሂደት የጸጥታ ማስከበር አካላት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ያስፈጽማሉ።
ከብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት፣ ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስ የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ሂደቱን በበላይነት እንደሚያስተባብር ታውቋል።
የክልል መንግሥታትም ተመሳሳይ ኮማንድ ፖስት አቋቁመው ሥራውን እንዲያከናውኑ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ገንዘቧን የሚወክል ምልክት እንዳልነበራት የተገለጸሲሆን በቅርቡ ለብር መለያ የሚሆን አዲስ ምልክት ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተገልጿል።