ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ኮሮናን በመከላከል ረገድ በአጭር ጊዜ ውሰጥ አመርቂ ሥራ አከናውናለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ ኮሮናን በመከላከል ረገድ በአጭር ጊዜ ውሰጥ አመርቂ ሥራ ማከናወኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ተናገሩ።

ለቫይረሱ መድኃኒት ለማግኘት በኢትዮጵያውያን የተጀመረው ጥረት የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ ተጠናቆ ወደ ላቦራቶሪ ሙከራ መሸጋገሩንም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ይህን ያሉት ዛሬ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የተገነባውን የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያ ማምረቻ ፍብሪካን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ነው።

ፋብሪካው በኢትዮጵያ መንግሥትና "ቢ.ጂ.አይ ሄልዝ ኢትዮጵያ" በተሰኘ የቻይና ኩባንያ ትብበር የተገነባ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በዚህን ወቅት በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ በተከሰተበት ወቅት ከሰዎች የሚወሰዱ ናሙናዎች ወደ ውጭ ሄደው ሲመረመሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በተካሄደው ሥራም ኢትዮጵያ በመመርመር አቅም በአፍሪካ ሶስተኛዋ አገር መሆን ችላለች ነው ያሉት።

እስካሁን ባለው ሂደት በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ መደረጉን በማስታወስ።  

አሁን ላይ ደግሞ ሳኒታይዘርና ማስኮችን ከማምረት ወደ መመርመሪያ መሳሪያዎች ምርት ተሸጋግረናል ነው ያሉት።

ፋብሪካው በዓመት 10 ሚሊዮን የመመርመሪያ መሳሪያዎችን እንደሚያመርትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ተናግረዋል።

ምርቱን ለአገር ውስጥ አገልግሎት ከማዋል በተጨማሪ "ሜድ ኢን ኢትዮጵያ" በሚል ጥራዝ ለውጭ ገበያ እንደሚውልም አብራርተዋል።

በተለይ በአፍሪካ የመመርመሪያ መሳሪያ የሚያመርቱ አገሮች ጥቂት በመሆናቸው ፋብሪካው ከኢትዮጵያ ባለፈ አፍሪካውያንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው ያብራሩት።

በተጨማሪም  በቅርቡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላቦራቶሪ ተቋቁሞ ትራንዚት ለሚያደርጉ መንገደኞች ምርመራ እንደሚደረግም አውስተዋል።

በከተሞችም ተጨማሪ ላቦራቶሪዎች ይቋቋማሉ ብለዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከሰትን እንደ እድል በመውሰድ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት በመጠቀም ረገድ አመርቂ ስራ ሰርታለች ነው ያሉት።

በአጭር ጊዜ በኢትዮጵያ የመመርመሪያ መሳሪያ ማምረት እንዲጀመር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አርከበ እቁባይን ጨምሮ ሌሎች ሚናቸውን ለተወጡ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

ፋብሪካው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲያበቃ የወባና ቲቢ መመርመሪያ መሳሪያዎችን እንደሚያመርትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ለቫይረሱ መድሃኒት ለማግኘት በኢትዮጵያውያን የተጀመረው ጥረት የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ ተጠናቆ ወደ ላቦራቶሪ ሙከራ መሸጋገሩንም ገልጸዋል።

ፈዋሽነቱ በላቦራቶሪ ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ሌላኛው የሙከራ ምዕራፍ እንደሚሸጋገርም ነው የጠቆሙት።

የለይቶ ማቆያና ህክምና ቦታዎችን የማደራጀቱና ማስፋቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም