አምባሳደር ኸርማን ኮህን አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ዕገዳ መጣሏ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ኸርማን ኮህን አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ዕገዳ መጣሏ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2/2013 (ኢዜአ) የቀድሞው የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር ኸርማን ኮህን አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ለጊዜውም ቢሆን ዕገዳ መጣሏ ተቀባይነት የሌለው ውሳኔ ነው አሉ።
የአሜሪካው "ፎሪን ፖሊሲ" መጽሔት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውኃ ሙሌት ተከትሎ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የመደበችው የ130 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዳይሰጥ ወስናለች በሚል ዘግቦ እንደነበር የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ጠይቆ አሜሪካ ልትሰጥ አቅዳ የነበረው ድጋፍ እንዳይሰጥ የተደረገው በጊዚያዊነት እንደሆነና የገንዘብ ድጋፉ የተያዘው ለአጭር ጊዜ መሆኑን መረዳቱን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ መግለጻቸው አይዘነጋም።
የቀድሞው የአሜሪካ አፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር ኸርማን ኮህን አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ዕገዳ የጣለችው "ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ግብፅ የያዘችውን አቋም እንድትቀበል ጫና ለማሳደር ነው" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
ይህ ውሳኔ "ስሜት የማይሰጥ" እንደሆነና አሜሪካ በሕዳሴው ግድብ ድርድር አለኝ የምትለውን የገለልተኛ አደራዳሪነት ሚና ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው ብለዋል።
የአሜሪካ ውሳኔ ኢትዮጵያ ይበልጥ በአቋሟ እንድትጠነክርና እንድትጸና የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።
አምባሳደር ኸርማን ኮህን በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው እ.አ.አ ከ1989 እስከ 1993 አገልግለዋል።
ከሣምንት በፊት ስድስት የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ዕገዳ መጣሉን ተቃውመው ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮና ለአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስቴቨን ሙኑሽን ደብዳቤ ማጻፋቸው የሚታወስ ነው።
ደብዳቤውን የጻፉት ኢልሃን ኦማር፣ ጄሰን ክሮው፣ ጆሀን ግራሜንዲ፣ ኮኒን አልሬድ፣ ጆይስ ቤቲ እና ጄራልድ ኮንሊይ ናቸው።
በደብዳቤው የድጋፉ ዕገዳ መጣሉ እጅግ እንዳሳሰባቸው የኮንግረስ አባላቱ የገለጹ ሲሆን ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሻክርና አሜሪካ በድርድሩ ያላትን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ይጥላል ብለዋል።
የአሜሪካ ውሳኔ በቀጠናው ካላት ፍላጎት ጋር የሚጻረርና ከ100 ዓመት በላይ የዘለቀው ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አባላቱ ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወጪ የሚገነቡት የጋራ ፕሮጀክትና ብሔራዊ ኩራት መሆኑ ይታወቃል።
በቀጠናው ለሚገኙ ሚሊዮኖች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ይገለጻል።
በመሆኑም ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍ መቋረጥ እንደሌለበትና ከግድቡ ድርድር ጋር ተያይዞ አሜሪካ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ የኮንግረስ አባላቱ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።