ቀጥታ፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በሀዋሳ ከተማ ለመቀበል ተዘጋጅተናል-- የከተማው ነዋሪዎች

ሀዋሳ ሀምሌ 6/2010 የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በኢትዮጵያዊ የእንግዳ መስተንግዶ ባህላቸው ለመቀበል መዘጋጀታቸውን በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በሀዋሳ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት በረከት አድነው  ኢሳያስ አፈወርቂ ሀዋሳ እንደሚመጡ ስትሰማ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማት ገልጻለች፡፡ "ኤርትራውያን ለጠቅላይ ሚኒስትራችን በአስመራ ከተማ ላይ ያደረጉት  የደመቀና ልባዊ አቀባበል በሀዋሳ ከተማ ለፕሬዚዳንታቸው  ለማድረግ ተዘጋጅተናል "ብላለች፡፡ "ኢትዮጵያዊያን እንግዳ የመቀበል ባህላቸው ዘመናትን የተሸገረ ነው " ያለችው ወጣቷ የኤርትራው ፕሬዝዳንትም ሆነ ልኡካን ይሄው አቀባበል እንደሚጠብቃቸው ተናግራለች፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ዳግም ወዳጅነትና አንድነትን በህይወት እያሉ ማየታቸው እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደግሞ አቶ መስፍን ገብሬ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡ የኤርትራ ፕሬዚዳንትና አብረዋቸው የሚመጡትን እንግዶች ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በጊዜ ሂደት እርቅ እንደሚያወርዱና ተጣልተው እንደማይቀሩ እምነት ቢኖራቸውም እንዲህ በቅርቡ ይሆናል ብለው እንዳላሰቡ  ተናግረዋል፡፡ " ተለያይን ላለፉት 20 ዓመታት ቢንቆይም እውነት ራሷን ገልጣ ተመልሰን ተገናኝተናል፤ በዚህም እድለኞች ነን "ብለዋል፡፡ በሃዋሳ በሚኖራቸው ቆይታም ከህዝቡ የኢትዮጵያዊያን ባህል የተንጸባረቀበት አቀባበል እንደሚጠብቃቸውና ለዚህም መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡ ሌላው  የከተማው ነዋሪ አቶ ምህረቱ ኤልያስ በበኩላቸው "የኢትዮጵያ መንግሥት ባሳየው ፍቅርና ይቅርታ የተገኘውን እድል በመጠቀም ፍቅራችንና ወዳጅነታችንን እናሳያለን፤ ኢትዮጵያዊያን በምንታወቅበት እንግዳ ተቀባይነት ባህል እናስተናግዳቸዋለንም "ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በታሪክ፣ በባህልና በመልከአ ምድር  ትስስር ያላቸው ህዝቦች በመሆናቸው  አንድነታቸው እንደሚመለስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡ ሃዋሳን ለጉብኝት እንደሚመጡ ሲሰሙ መደሰታቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪው በክብር ተቀብለው በፍቅር  እንደሚሸኟቸውም አመልክተዋል፡፡ በሃዋሳ ፒያሳ አካባቢ የሚኖሩት የ60 ዓመት እድሜ ያላቸው ወይዘሮ አይናለም አበበ በእድሜያቸው የሁለቱን ህዝቦች መቀራራብ እውን እየሆነ መምጣቱ ለማየት እድለኛ በመሆናቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ "እንግዳውን የምቀበለው ነጠላ አንጥፌ በምርቃት ነው፤ የከተማዋ ነዋሪ ሁሉ በጨዋነት ጠቅላይ ሚኒስትራችን በአስመራ የተደረገላቸውን አይነት አቀባበል ማድረግ አለበትም" ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም