የኢትዮጵያን ባህላዊ ምርቶች ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ እንሰራለን- አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ባህላዊ ምርቶች ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ እንሰራለን- አምባሳደሮች
አዲስ አበባ መስከረም 1/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ባህላዊ የአልባሳት ለዓለም ማህበረሰብ እንደሚያስተዋውቁ በተለያዩ አገሮች ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮች ተናገሩ።
ዱናሚስ የተሰኘ ኢትዮጵያ ሰራሽ ምርቶችን የሚያስተዋውቅ ድርጅት ለአምባሳደሮቹ ኢትዮጵያ ሰራሽ ባህላዊ አልባሳትን ሸልሟል።
አምባሳደሮቹ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያን በወከሉባቸው የዓለም ማህበረሰቦች ዘንድ ሰራሽ ምርቶች እንደሚያስተዋውቁ ገልጸዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ በጅዳ የኢፌዴሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ቆንስላ ጄኔራል አምባሳደር አብዱ ያሲን 'ኢትዮጵያ ሰራሽ' ምርቶችን በማስተዋወቅ ገበያ በመፍጠር ለስራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ፋይዳው የጎላ ነው።
ለምርቶቹ ገበያን እንደሚያፈላልጉ የገለጹት ዲፕሎማቶቹ፣አምራቾቹ በጊዜ፣ በዋጋና በጥራት ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ በኦማን የኢትዮጵያ አምባሳደር አይሮራት መሐመድና በዑጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዓለም ፀሐይ መሰረት ምርቶቹን በማስተዋወቅ ድርሻቸውን እንደሚወጡ አመልክተው፣ አምራቾቹ ብዛትና ጥራት ያለው ምርት ለማውጣት እንዲተጉ ጠይቀዋል።
በመሆም ሕብረ ብሔር የሆነችውን ኢትዮጵያ የባህል አልባሳት በተወከሉባቸው አገሮች በማስተዋወቅ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች አንዱ ተልዕኮ የኢትዮጵያን ባህልና ቱሪዝም ማስተዋወቅ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን ሰራሽ ምርቶችን ማስተዋወቅና መሸጥ ከአገር ገጽታ ባሻገር፤ ለአምራቹ ተጨማሪ ገቢ በማስገኘት ለሥራ ፈጠራ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቱ በአገር ልብስ መኩራት ከአምባሳደሮች መጀመር እንዳለበት ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ሰራሽ አልባሳትን የሚያስተዋውቀውን ድርጅት አድንቀዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የአገራቸውን ባህል መጠቀም፣ ማስተዋወቅና ገበያ ማፈላለግ ላይ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ለመላው ኢትዮጵያውያንም መልካም አዲስ ዓመትም ተመኝተዋል።