ቀጥታ፡

ዜጎች ለሰላምና ለአንድነት ዘብ በመቆም አገር መገንባት ይጠበቅብናል

አዲስ አበባ   መስከረም  1/2012 (ኢዜአ) የአገርን ሕልውና ለማስጠበቅና አንድነትን ለማጠናከር ዘብ መቆም እንደሚገባ የብሄር፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮች ገለጹ። 

በአዲስ አበባ ሸገር ፓርክ የብሄር/ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን የሚያንጸባርቀው ''የወዳጅነት አደባባይ'' ትናንት ተመርቋል።

በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የብሄር፣ብሄረሰቦች ተወካዮች በየቋንቋቸው የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፣አደባባዩ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በመዘከሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜ አገልግሎት ያነጋገራቸው የኦሮሚያ፣ የደቡብና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ተወካዮች እንዳመለከቱት ለኢትዮጵያ ብልጽግና መረጋገጥ ለሰላምና ልማት በጋራ መቆም ያስፈልጋል።

ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የመጡት የበርታ ብሄረሰብ ተወካይ አቶ ኢብራሂም ሲራጅ መንግሥት አገሪቱን ለማሳደግ ያለውን ራዕይ መሰነቁን ገልጸው፣ራዕዩን እውን ለማድረግ በጋራ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

አደባባዩ በአገሪቱ እኩልነት በተግባር እየተገለጠ መምጣቱን ማሳያ ሆኖ እንዳገኙትም ተናግረዋል።

ከደቡብ ክልል የወላይታ ብሄረሰብን ወክለው የመጡት አቶ ኢያሱ ደጃቦ በበኩላቸው ሕዝቡ አገራዊ  ለውጡን በማስቀጠል ለብልጽግናው ጉዞ የራሱን አሻራ ማስቀመጥ አለበት ነው ያሉት።

ትውልዱ ያሉትን በጎ ነገሮች በማስቀጠል ለመጪው ትውልድ አዲስ ታሪክ ሰርቶ ማስረከብ እንደሚገባውም ገልጸዋል።                                                          

ከደቡብ ኦሞ ኛንጋቶም ብሄረሰብ የመጡት አቶ አብዲሳ ዩቱክ ደግሞ፤ ወጣቶች ለሚያለያዩ ኃይሎች ጆሮ ሳይሰጥ አንድነትና ህብረቱን አስጠብቆ ለሰላምና ብልጽግና ተግቶ መስራት አለበት ብለዋል።

አገርን ወደ ኋላ ከሚያስቀር  ድርጊቶች በመታቀብ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ከኦሮሚያ ጉጂ ብሄረሰብ የመጡት አቶ ታደሰ ሀዲማ ወጣቶች አገራቸውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት እንዲተጉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም