ቀጥታ፡

አዲስ ዓመት በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ዕይታ

  አዲስ አበባ   መስከረም  1/2012 (ኢዜአ) ወደ አዲስ ዓመት ስንሻገር በአዲስ እሳቤ የ2012 ጉድፎችን አራግፈን መሆን አለበት --- የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች

በራሷ የዘመን ቀመር በምትቆጥረው ባለ13 ወርኅ ፀጋዋ ኢትዮጵያ ከልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ዘመኑ ዛሬ 2013 ዓመት ይሆናል።

ዘመን ሲለወጥ ሰዎች አሮጌውን ዓመት አሻግሮ ለአዲስ ዓመት ላበቃቸው እያመሰገኑ አዳዲስ ህልሞችን ማለም፣ ብሩህ ተስፋና ዓመት መመኘት የዘወትር ልማድ ነው።

በተለይ እንደ 2012 ብዙ መጥፎ ጠባሳዎችን ጥሎ የሚያልፍ ዓመት ሲሆን፣ በመጪው ዓመት ብሩህ ተስፋ መመኘትም ላቅ ያለ ስፍራ አለው።

ክረምቱ ሲሸኝ፣ የጥቢ ወርኅ ሲብት የተፈጥሮው ሁናቴ፣ የመሰኩን ልምላሜና የነገን ተስፋ በመያዝ የሚደረገው የአዲስ ዓመት ኑባሬ በኪነ ጥበብ ዓለም ውስጥ ''ትልቅ'' ስፍራ ይሰጠዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም 2012ን ስንሻገር በዓመት ጉድፎችን አራግፎ መሻገር ተገቢ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ታዋቂው ሙዚቀኛ ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) "ዘመን ሲለወጥ በምንሸኘው ዓመት ካሳለፍናቸው መጥፎ ድርጊቶች በመማር የአስተሳሰብ ለውጥ በማድረግ መተሳሰብ፣ መፈቃቀርና ለዕድገት መስራት ይገባል" ይላል።

የፊልም ባለሙያዎች አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉና አርቲስት የትናየት ታምራትም በ2012 ኢትዮጵያ ያሳለፈቻቸው ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሁነቶች በአዲሱ ዓመት እንዳይደገሙ ምኞታቸውን ይገልጻሉ።

የቀደምት ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች በአዲሱ ዓመት ልንኖራቸው እንደሚገባም ገልጸዋል።

ለአዲሱ ዓመት መልካም ምኞታቸውንም ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙ "የኢትዮጵያውያን ነባር ዕውቀቶች እየተፋቱ፣ ማህብራዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ ዛሬ ላይ ወንድም በወንድሙ የሚጨክንበት መጥፎ ጊዜ ላይ ደርሰናል" ይላል ።

ለዚህ ማሳያም ባለፈው ዓመት የተከሰቱ መጥፎ ሁነቶች ''ትልቅ'' ማሳያ መሆናቸውን ገልጾ፤ መሰል መጥፎ ድርጊቶች በቀጣይ እንዳይደገሙ በሥነ ጽሁፍ ጥበብ ላይ አተኩሮ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክቷል።

ቀደምት የሥነ ጽሁፍ ሰዎች እንዳደረጉት ሁሉ በኢትዮጵያዊነት፣ በህዝብ አብሮነትና አንድነት ላይ ደራሲያንና ገጣሚያን መትጋት እንዲተጉም ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም