ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር እራሱና ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ሊሆን ይገባል

ባህርዳር፣ ደሴ፣  ጳጉሜ 5/2012 ( ኢዜአ) ህብረተሰቡ የዘመን መለወጫ በዓልን ሲያከብር እራሱንና ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባለፈው ዓመት ካስመዘግብናቸው ስኬቶች ባሻገር የኮሮና በሽታ መከሰት ትልቅ ስጋት ሆኖ ነበር ብለዋል።

በሽታው  ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገር የጤና ባለሙያዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና ባለሃብቶችን ያሳተፈ ተግባር መከናወኑን አውስተዋል።

የአፍና  አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መልበስም ኮሮናን እስከ 65 በመቶ መከላከል እንደሚቻል በዓለም ላይ የወጡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ጠቁመው ህብረተሰቡ የበዓል ግብይት ሲፈጽም ጭንብል መጠቀምና  ሌሎችንም  ጥንቃቄዎች ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

የክልሉ የሰላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር መንገሻ አውራሪስ በበኩላቸው በየደረጃው የሚገኘው የፀጥታ ኃይል ጭንብል የማያደርጉትን በመከታተል እንዲጠቀሙ የመቆጣጠር ስራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሰይድ መሐመድ ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር እራሱንና ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ በጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

የስራ ኃላፊዎቹ  አዲሱ ዓመት መላው የአማራና የኢትዮጵያ ህዝቦች አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ አንድነት የሚጠናክርበትና  እድገት የሚፋጠንበት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም