ቀጥታ፡

የኮቪድ-19 መከሰትን ተከትሎ ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝ አቅመ ደካሞችን መደገፍ ይገባል

ሐረር፣ ጷጉሜን 5/2012 (ኢዜአ)  የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝና በዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖሩ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል የኤች አይ ቪ/ኤድስ መቆጣጠሪያ ሴክሬተሪያት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

ጽሕፈት ቤቱ ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝ 750 አቅመ ደካማ ወገኖች የአንድ ወር የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ዛሬ አድርጓል።

የሴክሬተሪያቱ ኃላፊ ወይዘሮ ፈርያ መሀመድ በልገሳው ላይ እንደተናገሩት ይህ ወቅት ኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ባሻገር መደጋገፍንና መተጋገዝን የሚጠይቅ ነው።

“በዚህም በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ተፅዕኖ ለጉዳት የተዳረጉ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ ወገኖችን መደገፍ ተገቢና በተለይም ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ለችግር ለተዳረጉ ወገኖች በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የማኮሮኒ፣ የምግብ ዱቄትና ዘይት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በክልሉ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ለሚገኙ ዜጎች የሚደረገው የድጋፍ ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የሐረሪ ክልል የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል የሀብት አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም በበኩላቸው እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በበርካቶች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ ነው።

በተለይም ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የተለያዩ ተጓዳኝ በሽታዎች ያሉባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊደርስባቸው ከሚችል ተፅዕኖ ለመታደግ የድጋፉ ሥራ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸው ይህም ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ድጋፉ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ዘላለም ጥሩሰው እንደገለጹት ለተጓዳኝ በሽታዎች ተጋላጭ እንደመሆናቸውና ሥራም የማግኘት እጥረት እያጋጠማቸው ስለሚገኝ የምግብ እህል ድጋፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ድጋፉን ላደረገላቸው ተቋም ምሥጋና ያቀረቡት ወይዘሮ ዝናሽ ፈለቀ በበኩላቸው የምግብ እህል ድጋፉ በአሁኑ ወቅት ያጋጠማቸውን ወቅታዊ ችግር ለማለፍ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

ከምግብ ቁሳቁስ ድጋፉ ባሻገር የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝ ወገኖች ቤት ለቤት በመሄድ ድጋፍ ለሚያደርጉ 132 በጎ ፍቃደኞች የግል ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ደጋፍ ተበርክቷል።

የኮሮና ቫይረስ መግባትን ተከትሎ በተፈጠረው የእንቅስቃሴዎች መዳከም ምክንያት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉና የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ለችግር በመጋለጣቸው የክልሉ ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ሴክሬታሪያት ድጋፍ የሚቀጥል መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም