ቀጥታ፡

ለአገር ባለውለታ አንጋፋ አትሌቶች እንክብካቤና ድጋፍ ሊደረግ ይገባል

አዲስ አበባ፣ 3/2012 (ኢዜአ) ለአገር ባለውለታ አንጋፋ አትሌቶች ተገቢው ድጋፍና እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተገለፀ።

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአንጋፋ አትሌቶች የማዕድ ማጋራትና በቦሌ ክፍለ ከተማ ላሉ ለችግር ለተጋለጡ  የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አድርጓል።

ሴት ልጅ ቁምጣ ለብሳ አደባባይ ከወጣች 'ታሰድባለች' በሚባልበት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ሩጫ የጀመሩት አትሌት ፅጌ ገብረመሲህ፤ በትምህርት ቤቶች ውድድር ለሁለት አመታት ሪከርድ በማሻሻል በአገር ደረጃ መሸለማቸውን ያስታውሳሉ።

በአለም መድረኮችም አገራቸውን ወክለው የተወዳደሩት እኚህ አንጋፋ አትሌት በአሰልጣኝነትም አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ይናገራሉ።

ለሰሩት ተግባርና ላበረከቱት አስተዋፅኦ የሚገባቸውን ክብር እንዳላገኙ በመግለጽ፤ ለአገር ባለውለታ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ስፖርታዊ ውድድሮች በሚደረጉበት ጊዜም የአገር ባለውለታዎች በክብር እንግድነት ተጋብዘው መገኘት እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቶች 'አረንጓዴ ጎርፍ' የሚለውን ስያሜ ባገኘበት ዘመን በስፔን አገራቸውን ወክለው የተሳተፉት ሻለቃ ባሻ ግርማ ወልደሃና በተለያዩ አገሮች ተወዳዳሪ ሆነው እንደተሰለፉ ገልፀዋል።

ነገር ግን እንደ አገር ባለውለታነታቸው በጡረታ ከተገለሉ በኋላ ትኩረት መነፈጋቸውን በመግለጽ ለአገር ባለውለታዎችን መንከባከብና የሞራል ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አስረድተዋል።

በዛሬው እለትም ለተደረገላቸው የማዕድ ማጋራት ምስጋናን ችረዋል።

የአዲስ አበባ አንጋፋ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወገኔ ሲሳይ እንዳሉት፤ አገር ወክለው የተወዳደሩ አትሌቶች በአሁኑ ሰዓት በዘበኝነትና መሰል ስራ እየተዳደሩ ነው።

''አሁን ደግሞ ኮሮናቫይረስ በመከሰቱ ችግር ላይ ወድቀዋል'' ብለዋል።

በአንዳንድ ባለሃብቶች ከሚደረግላቸው ድጋፍ እየተዳደሩ መሆናቸውን አንስተው፤ የአገር ባለውለታ የሆኑ አንጋፋ አትሌቶችን ባለድርሻ አካላት ቢመለከቷቸውና ለነሱ የሚሆን የክብር ስፍራና የገቢ ማስገኛ መፈጠረ እንዳለበት አመልክተዋል።

በተለያዩ ክለቦችች በዋና አሰልጣኝነት ያገለገሉትና በርካታ አትሌቶችን ለአገሪቱ ማበርከታቸውን የሚገልፁት የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሱ አለማየሁ የማህበሩ አላማ ለችግር የተጋለጡ አትሌቶችን ማሰባሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለያዩ የአለም መድረኮች የተሳተፉ 150 አትሌቶች በማህበሩ ውስጥ እንዳሉ ገልፀው፤ ማህበሩ ኮሮናቫይረስ ከገባ በኋላም አቅም ላጡትና ለተቸገሩት ድጋፍ ማደረጉን አስረድተዋል። 

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መልካሙ ተገኝ ''ኮሮናቫይረስን ለመከላከል እንደግለሰብ የሚጠበቅብኝን ለመወጣት ድጋፍ አድርጌያለሁ'' ብለዋል።

በዚህም ለአገራቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አትሌቶች ማዕድ ማጋራታቸውንና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ለሚገኙ ችግረኛ የማህበረሰብ ክፍሎች የምግብ ግብአት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

''ከዚህ ቀደምም ከፌዴሬሽኑ ጋር በመሆን የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸውን አስታውሰው በቀጣይም ኮሮቫይረስን ለመከላከል የማደርገውን ድጋፍ እቀጥላለሁ'' ብለዋል።

የቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 12 አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አንዋር መሀመድ እንዳሉት፤ ወረዳው እስከትናንት ድረስ ከ700 በላይ ለሆኑ የወረዳው ነዋሪዎች በዓሉን ምክንያት በማድረግ ማዕድ የማጋራት መርሃግብር ተደርጓል።  

በዛሬው እለት ከአትሌት መልካሙ ጋር በመሆኑ በወረዳው ውስጥ ወረገኑ በሚባለው አካባቢው ላሉ ለተቸገሩ ሰዎች ማዕድ የማጋራት መርሃግብር ተከውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም