ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ጳጉሜ 5/2012 (ኢዜአ) በአዲሱ ዓመት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሁሉም መስክ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት አዲሱን ዓመት አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ነው።
ፕሬዝዳንቷ በመልዕክታቸው "ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን የትም እንሁን የት ለአገራችን ልናበረክተው የምንችለው ድንቅ ነገር አለን፤ ሃላፊነታችንን በአግባቡ ለመወጣት እንነሳ" ብለዋል፡፡
በ2012 ዓመት በአገሪቱ በተከናወኑ ታላላቅ የልማት ስራዎች ህብረተሰቡ ላደረገው ተሳትፎ አድናቆታቸውን ገልጸው በቀጣዩ ዓመትም ይህ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አሳስበዋል።
ለዚህም ህብረተሰቡ ከኮሮና ቫይረስ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበው ለጋራ ዕድገት አገራዊ አንድነትና መግባባትን ማጠናከር እንደሚገባ ነው የመከሩት።
"አዲሱ ዓመት የሰላምና የልማት ተስፋዎቻችንን የምናፋፋበት ፤ የምናድግበት ፤ ችግሮቻችንን የምንቀርፍበት ፤ ግጭትና አለመግባባት ሳይሆን ምክንያታዊነትና መደማመጥ የሚንሰራፋበት ዓመት እንዲሆንልም ምኞቴን እገልጻለሁ" ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት
በሀገር ውስጥና በየትኛውም የዓለም ክፍል የምትገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ፣
ከጥቂት ሰዐታት በኃላ 2012 ዓመተ ምህረትን ላይመለስ ተሰናብተን 2013ን እንቀበላለን፡፡
እንኳን ለ2013 አዲስ ዓመት አደረሳችሁ ፣ ዓመቱ የሠላም ፤የጤና ፤ የአንድነትና የእድገት እንዲሆንልን ምኞቴን መግለጽ እወዳለሁ፡፡
እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ ስል በዚህ ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸውን ያጡና ይህችን ቀን ለማየት ያልታደሉ ወገኖቻችንን በማሰብ ጭምር ነው፡፡
አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር አዲስ ህልምና ተስፋ የምንሰንቀው በተለምዶ የሚደረግ ስለሆነ አይደለም ፡፡ አዲስ ዓመት የአዲስ ዕይታ ምንጭ ነው ፡፡ በነበረውና በሚሆነው መካከል ትስስር የሚፈጥርልን ድልድይ በመሆኑ ነው፡፡
ከድክመቶቻችን ፤ ስህቶቻችን ከተማርን መውደቅን በመነሳት ፤ መክሸፍን በስኬት ለማካካስ ትልቅ ጉልበት ስለሚሆነን ጭምር ነው፡፡
2012 ነገን በተስፋ እንድናይ የሚያደርጉን መልካም ነገሮችን አይተንበታል ሰምተንበታል፡፡ የሁላችንም የልብ ትርታ ያረፈበት የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሀ ሙሌትን አሳክተናል፡፡ እጅግ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻዎችን እንዲሁም ተጽኖዎችን ተቋቁመን ለዚህ በቅተናል፡፡
ኢትዮጵያውያን በያለንበት ፤ በተሠማራንበት ሙያ ፤ ባለን እውቀትና አቅም ተባብረን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን ፡፡ ሂደቱ ብዙ ነገሮችን አስተምሮናል ብየ አምናለሁ፡፡ ዘንድሮ በግድቡ ላይ የምንሰራው ተግባር ለአጠቃላዩ ውጤት ወሳኝ ነውና መላው ኢትዮጵያውያን በያላችሁበት ለዚህ ስኬት የተለመደውን ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪየን አቀርባለሁ፡፡
በዓመቱ አጋማሽ ገደማ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ህዋ መላካችን ፤ እጅግ በሚያሥደምም ሁኔታ መላው ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበትና 5 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል የተቻለበት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻም በኩራት ከምንናገራቸው መልካም ተግባሮቻችን መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን እምርታዎችን ማስፋትና ማጉላት ይገባናል፡፡ በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ ወደኃላ የምንለው አቅም ፤ ተነሳሽነት ፤ ሀብት እና እውቀት መኖር የለበትም።
ከነዚህ በጎ ሥራዎች ጎን ለጎን በ2012 እጅግ ክፉ አጋጣሚዎችንም አሳልፈናል፡፡ ብስራትና እንቅፋት ተፈራርቀውብናል ፡፡ ዛሬና ትናንትን ባስተናገድንበት መንገድ ነገን መዝለቅ እንደማንችል ሁነኛ ትምህርት ያገኘንበት ዓመት ነው ብየ አምናለሁ፡፡
ከመጋቢት መጀመሪያ ጀምሮ እየተስፋፋ የመጣው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሀገራችን ከተከሰተ ወዲህ በሌሎች የአለም ክፍሎች ያስከተለው ጉዳት በእኛም ላይ እንዳይሆን እንደ ሀገር የሚቻለንን ስናደርግ ቆይተናል ፡፡
ወረርሽኑ ወደ ሀገራችን ከመግባቱ በፊት የነበረውን የእፎይታ ጊዜ በመጠቀም አቅም የፈቀደው ዝግጅት በመንግስት በኩል ተከናውኗል፡፡
በዋናነት ህብረተሰቡ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ የህክምና ምክሮችን በማስተላለፍ ፤ ማህበራዊ ንቅናቄዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ በተለይም በበሽታው የተነሳ ሊፈጠር የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና በጋራ ለመከላከል ርብርብ ተደርጓል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ወረርሽኙ ሊያሥከትል ይችል የነበረውን መዘዝ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይሁንና በወረርሽኙ የመጀመሪያ ወራት የታየው የተጠናከረ እንቅስቃሴ እየላላ መሄዱ ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል፡፡ የምናየው የህብረተሰቡ መዘናጋት በጣም አስጨናቂ ነው ፡፡ ወረርሽኙ የጠፋ እስኪመሰል ድረስ ዜጎች ወደ ድሮው ማህበራዊ ግንኙነቶቻቸው ሲመለሱ ይታያል ፡፡
ክስተቱ የማህበረሰባችንን ህግ አክባሪነት ባህል ብዙ የሚቀረው እንደሆነም አሳይቶናል፡፡
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም ላይ ጥሩ ለውጥ እየታየ ቢሆንም አጠቃቀማችን ግን ከህክምና ባለሙያዎች መመሪያ በአግባቡ አለመከተል ይታያል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል ከተቀመጡት አራቱ የመከላከያ መንገዶች መካከል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ መጠቀም ዋና ተመራጭ ነው ፡፡
በቅርቡም በሀገራችን ይፋ የተደረገው የ"ማስክ ኢትዮጵያ" የአንድ ወር ዘመቻ ወረርሽኙ ከቁጥጥራችን ውጭ እንዳይወጣ ለምናደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ሁነኛ ክንዳችን ነው፡፡
ዘመቻው የመጨረሻው ውጤት አይደለም፡፡ የምንፈልገው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛን ህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀም በማድረግ ወረርሽኙ የሚዛመትበትን መንገድ መዝጋት ነው ፡፡
ሁላችንም የሚገባንን እናድርግ ፤የችግሩ ምክንያት ከመሆን ይልቅ የመፍትሄ አካል እንሁን፡፡
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በ2012 ዓ.ም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ካስከተለብን ችግር በላይ የዜጎቻችንን ውድ ህይወት ተቀጥፏል፡፡ እስከዚህ ድረስ ለምን ተጨካከን? ብለን በግልጽ ፤ በሀቅ መነጋገር ፤መወያየት ይኖርብናል ፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት እጅግ ክቡር ነው፡፡ መርከስ የለበትም፡፡
በምንም መልኩ ለእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ፊት መስጠት አይገባንም ፡፡ በሀሳብ ፤ በአመለካከት መለያየት ያለና የሚኖር ጸጋ ነው ፡፡ ዴሞክራሲን ያጠናክራል እንጂ በተጻራሪው መታየት የለበትም ፡፡
ሁላችንም የዚህች ሀገር ባለቤቶች ነን፡፡ የሀገራችን ጉዳይ በእኩል መጠን ያገባናል ፤ ይመለከተናል ፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የትም እንሁን የት ለሀገራችን ልናበረክተው የምንችለው ድንቅ ነገር አለን፡፡ ይህን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንነሳ፡፡
በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላምና የልማት ተስፋዎቻችንን የምናፋፋበት ፤ የምናድግበት ፤ ችግሮቻችንን የምንቀርፍበት ፤ ግጭትና አለመግባባት ሳይሆን ምክንያታዊነትና መደማመጥ የሚንሰራፋበት ዓመት እንዲሆንልም ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡
በድጋሚ እንኳን ለ2013 አዲስ አመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ፤ አደረሰን
መልካም አዲስ ዓመት
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ፡፡