ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከ800 በላይ የነዳጅ ማደያዎች ሊገነቡ ነው

ባሕርዳር፣ ጳጉሜ 5/2012 (ኢዜአ) አማራ ክልል በየጊዜው የሚፈጠረውን የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለማቃለል ከ800 በላይ ማደያዎች እንደሚገነቡ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ ከሚካሄደው ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ አኳያ ከሚቀርበው ነዳጅ ጋር ባለመመጣጠኑ እንቅፋት ሆኗል።

በክልሉ ከመቶ ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ቢኖሩም የባጃጅ፣ የሞተር ብስክሌት፣ የመስኖ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችና የገጠር ወፍጮዎች ቁጥር መጨመር ለነዳጅ አቅርቦቱ አለመመጣጠን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል።

ችግሩን ለመፍታት ቢሮው ባካሄደው ጥናት የነዳጅ ማከፋፈያ መሠረተ ልማት አለመኖርና የነዳጅ ማደያ ቁጥር ማነስ  በዓመት ወደ ክልሉ የሚገባው ነዳጅ ከ300 ሚሊየን ሊትር በታች እንደሆነ አረጋግጧል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አንድ መቶ የሚሆኑ የነዳጅ ማከማቻና ማከፋፋያ ዲፖዎችን ለማስገንባት በተካሄደ እንቅስቃሴ 115 ባለሀብቶች ያቀረቡትን የሥራ ዕቅድ በመገምገም የድጋፍ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በክልሉ የሚያስፈልገው ከ አንድ ሺህ በላይ የነዳጅ ማደያዎች ቢሆኑም እስካሁን አገልግሎት የሚሰጡት 202 ብቻ እንደሆኑ በጥናት በማስደገፍ ለክልሉ ምክር ቤት መቅረቡን አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ የቀረበለትን  ጥናት አይቶ የነዳጅ ማደያዎችን ለማበራከት ከነሐሴ 30/2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 30/2013 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የማስፈጸሚያ መመሪያ አውጥቷል ብለዋል።

በመመሪያው መሠረትም ከ800 በላይ የነዳጅ ማደያዎች በሁሉም የክልሉ ዞን፣ ከተማ አስተዳደርና የወረዳ ማዕከላት ለማስገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ይህም ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች  የሚመጡ ባለሀብቶችን በማሳተፍ እንደሚካሄድ ያመለከቱት የቢሮው ምክትል ኃላፊ የባንክ ካፒታል፣ በዘርፉ ያላቸው ልምድና ሌሎች መሥፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድምነው ክንዱ በበኩላቸው በነዳጅ ማደያ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ገንብተው ወደ ሥራ መግባት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።

ለዚህም ከ1 ሺህ 600  እስከ 2 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ በሊዝ መነሻ ዋጋ በመስጠት የናፍጣ፣ ቤንዚንና ነጭ ጋዝ ታንከሮችንና ተጓዳኝ መገልገያዎችን መገንባት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በሁሉም ከተሞች የሚገኙ አስተዳደሮች በመመሪያው መሠረት መሥፈርቱን ለሚያሟሉ ባለሀብቶች ቦታ በመስጠት ክልሉ የያዘውን ግብ ለማሳካት በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ባለሀብቶችም ግንባታውን አጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሳይጀምሩ ለሦስተኛ ወገን በሽያጭም ሆነ በሌላ መንገድ ማዘዋወር እንደማይቻሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም