የሃይማኖት አባቶች 'እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ' ሲሉ የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት አባቶች 'እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ' ሲሉ የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5/2012 (ኢዜአ) የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አባቶች 'እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ' ሲሉ የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላለፉ።
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሆን ተመኝተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹ አቡነ ማቲያስ አዲሱን አመት አስመልክተው ባስተላለፉት የ'እንኳን አደረሳችሁ' መልእክት ''አዲሱን አመት አንድ ብለን ስንጀምር ያለፈውን ዓመት ለአፍታ ቆም ብለን ማሰብ የሚኖርብን ነው'' ብለዋል።
ባለፈው አመት የተከሰቱትን ድክመቶች በአዲሱ ዓመት ላለመድገም ቁርጥ ውሳኔ በማሳለፍ ወደ ስራ መግባት የሚያስፈልግበት እንደሆነ አመልክተዋል።
''ኢትዮጵያ አብያተ ሃይማኖት የማይቃጠሉባትና የማይደፈሩባት፣ ዜጎች የማይገደሉባት፣ የማይፈናቀሉባትና የማይሰጉባት አገር እንድትሆን እያንዳንዱ ሰው ቃልኪዳን መግባት አለበት'' ብለዋል።
''ይሕ እውን ሊሆን የሚችለው አስተማማኝ ሰላም ሲኖር ነው'' ያሉት ፓትርያርኩ አስተማማኝ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሲሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም ሁሉም አካላት ስለ ሰላምና ስለ ሀገር አንድነት፣ ስለዜጎች እኩልነትና ስለጋራ ጥቅም አንድ ላይ ሆነው በጥልቀት ተመካክረው በሚፈጥሩት መግባባት እንደሆነም ጠቁመዋል።
''ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በዚሁ ዙሪያ በአዲሱ ዓመት በአጽንኦት እንዲያስቡበት እንመክራለን ፤ የእልህ የበቀል አመለካከት አገራችንን ዋጋ እንዳያስከፍላትም መጠንቀቅ አለብን'' ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እድሪስ በበኩላቸው አዲሱ ዓመት ህብረተሰቡ የሚጠቅመውን በመውሰድ የሚጎዳውን የሚተውበት ዓመት እንዲሆን ባስተላለፉት መልዕክት ተመኝተዋል።
ያለፈው ዓመት በርካታ ጥሩም መጥፎም ነገሮች የተስተናገዱበት እንደነበር አስታውሰዋል።
''በ2012 የሰው ልጅ በርካታ ፈተናዎች ያለፈበት መሆኑን አይተናል'' ያሉት ሀጂ ዑመር፤ ይህን ፈተና በጽናት ማለፍ እንደተቻለው ሁሉ ቀጣዩ ዓመት የመተሳሰብ፣ የመፈቃቀርና የመተጋገዝ እንዲሆን ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
ለኢትዮጵያ ሰላምና እድገት ወሳኙ ቤተሰብ መሆኑን አውስተው፤ ቤተሰብ ልጆቹን በስነ-ምግባር በማነፅ ትልቅ ሀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣዩ ዓዲስ አመት ስብእናው የተስተካከለ ትውልድ ለማፍራት ከመምህራን ብዙ እንደሚጠበቅ ያስታወሱት ሀጂ ኡመር፤ ወጣቱ ከስሜታዊነት ርቆ በአስተውሎት እንዲጓዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለይ የሀይማኖት አባቶች ከስልጣን፣ ከኩራትና ከገንዘብ በመራቅ የሀይማኖት አባትነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ተወዳጅ፣ ተፈላጊና የሚከበሩ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በመንግስት ሀላፊነት ላይ ያሉ አመራሮች በእኩልነት ህዝቡን የሚያገለግሉበት ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የፍቅር የመቻቻል የእድገት ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ-ኢየሱስ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ ለሁላችን መኖሪያና መገለጫ ጥላችን ሆና ኖራለች፤ ትኖራለችም" ሲሉ ገልጸዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ-ኢየሱስ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞትን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት "አዲሱን ዓመት በተስፋ ተሞልተን ልንቀበለው ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡
"ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያላቸው እምነት ፍጹም እንደሆነው ሁሉ እኛም በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ፍጹም ሊሆን ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ዜጋ ለሰው ማሰብና መኖር እንዳለበትም ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ-ኢየሱስ አስገንዝበዋል፡፡
"በትክክል፣ በእውነት ተዛምዶ፣ በጋራ ዓላማ፣ መመሪያና ፍላጎት ኑሯችንን ከጭንቀትና ሃሳብ አውጥተን በሰላም የምንኖርበትና የምንቀሳቀስበት የደስታ ዓመትና ጊዜን እግዚአብሔር እንዲሰጥ ተግተን ልንለምን ይገባል" ሲሉም አባታዊ ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ፈጣሪውን የሚወድ ሁሉ "ክፉን ነገር ጥሉ" ሚለውን የአምላክ ቃል መርሳት እንደሌለበትም አስገንዝበዋል፡፡
"መንግስት የዜጎቹ ከለላና ጠበቃ ነው" ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ-ኢየሱስ፤ የዜጎችን ደህንነትና በሰላም የመኖር ዋስትና ሊያረጋግጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የአሁኑ ትውልድ በአንድነትና በህብረት በመቆም ለመጪው ትውልድ መልካም ነገር ሰርቶ የተሻለች ኢትዮጵያን ማቆየት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
በኮቪድ-19 ምክንያት ተቸግረው በቤት ውስጥና በጎዳና ላይ የሚገኙ ወገኖችን በተቻለ አቅም ሁሉ ማገዝና መርዳት አስፈላጊ መሆኑንም መክረዋል፡፡
አዲሱ ዓመት የዘርና የጎሳ ተቃርኖ የሚጠፋበት ዓመት እንዲሆንም ተመኝተዋል።
"ዓመቱ ሁሉም እርስ በርስ የሚዋደድበትና የሚተሳሰብበት፣ የምህረትና የይቅርታ መንፈስ የሚሞላበት፣ ኮሮናቫይረስ ከኢትዮጵያና ከዓለም የሚወገድበት እንዲሆን ተግቶ መጸለይ ይገባል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ምክትል ፕሬዚዳንት ቄስ ዶክተር ኪሮስ ላቀው በመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸው አዲሱ ዓመት ዜጎች በመቻቻል፣ በአብሮነትና ጥላቻን በማስወገድ እንዲቀበሉና ለአገራዊ አንድነት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጠናቀቀው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ በጎም መጥፎም ነገሮች ተስተውለው እንደነበር አስታውሰው፤ በዓመቱ በርካታ አዳዲስና ተስፋ ሰጪ ነገሮች የታዩበት እንደሆነም ገልጸዋል።
"ህዝበ ክርስቲያኑ የ2013 ዓመትን በአዲስ ተስፋና በመልካም እሳቤ ሊቀበል ይገባል" ብለዋል።
ለዚህም ጥላቻን በማስወገድ በመቻቻል፣ በአብሮነትና በአዲስ መንፈስ ህይወትን መጀመር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ ልብን ንጹህ ማድረግና ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ችግሮች እንዲፈቱ መንግስት ከማህበረሰቡ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ አካላት ጋር ሰላማዊ ውይይቶችን በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት እንዳለበትም ነው የገለጹት
ቤተክርስቲያኗም አልፎ አልፎ እርስ በርስ እየተስተዋለ ያለውን አለመግባባትና ልዩነቶች ለመፍታት አበክራ እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።