ቀጥታ፡

ማረሚያ ቤቶች የዘመን መለወጫ ኮቪድ-19 መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ ያከብራሉ - ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ጳጉሜ 5/2012 (ኢዜአ) ማረሚያ ቤቶች የዘመን መለወጫ በዓልን ኮቪድ-19 መከላከል መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚያከብሩ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ጀማል አባሶ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት በዓሉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከግምት ውስጥ  ባስገባ መልኩ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል።

ታራሚዎች በዓሉ ሲከበር አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲያከብሩ መሰራቱንም  ተናግረዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል የታራሚ ቤተሰቦች ከታራሚዎች እንዳይገናኙ ክልከላ መደረጉንም ገልጸዋል።

በዓሉን ታሳቢ ባደረገ መልኩም ታራሚዎች ቤተሰቦቻቸውን በስልክ እንዲገናኙ እንደሚደረግ ኮሚሽነር ጄኔራል ጀማል አስታውቀዋል።

ለታራሚዎች ለበዓል መዋያ ከመንግሥት፣ ከግለሰቦችና ከተለያዩ አካላት የተሰበሰበ ድጋፍ እንደሚበረከትላቸውም ገልጸዋል።

በዓሉን በማስመልከት ዕድሜያቸው የገፉ፣ የጤና እክል ያለባቸውና ከዚህ በፊት በይቅርታ ከተፈቱት ውስጥ ያልተካተቱ 78 ታራሚዎች ትናንት በይቅርታ መለቀቃቸውን ጠቁመዋል።

አቶ ጀማል  አዲሱ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የደስታ፣ የሰላም፣የብልጽግናና የስኬት እንዲሆን ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም