በአዲሱ ዓመት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ሁሉም በጋራ እንዲሰራ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ሁሉም በጋራ እንዲሰራ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ጳጉሜ 5/2012 (ኢዜአ) በአዲሱ ዓመት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል መላው ህዝብ የጋራ ርብርብ እንዲያደርግ የጤና ሚኒሰትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።
የጤና ሚኒስቴር አዲስ ዓመትን በማስመልከት ለጤና ባለሙያዎች፣ ለሚኒስቴሩ ሰራተኞች ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የ2012 ዓ.ም ሚኒስቴሩ በርካታ ስኬቶችን ያከናወነበት ፈተናዎችም ያጋጠመበት ዓመት ነበር።
ሚኒስቴሩ ያወጣው የአምስት ዓመት እቅድ የሚገባደድበት ዓመት ስለነበር በርካታ ሥራዎች የተደራረቡበት ጫና የነበረበት ዓመትም እንደነበር ገልጸዋል።
በዓመቱ አጋማሽ አካባቢ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ደግሞ ትልቅ ፈተና መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም የጤና ባለሙያዎች ይህንን ቫይረስ ለመከላከል ፊት ለፊት በመጋፈጥ ትልቅ ተጋድሎ እየፈፀሙ መሆናቸውን አንስተው ምስጋና ቸረዋቸዋል።
በሌላ በኩል በነዚህ ጊዜያት ውስጥ መልካም ልምዶች የተቀመሩበት በተለይም በጋራ መሥራት ምን ያክል ጥቅም እንዳለው ግንዛቤ የተያዘበት እንደነበር አንስተዋል።
በ2013 ዓ.ም አዲስ ተስፋ በመሰነቅ የተጀመሩት ሥራዎች የሚጠናከሩበት ለተሻለ ውጤት የሚሰራበት እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ ወረርሺኙን ለመከላከል ይበልጥ በጋራ የሚሰራበት ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል።
ኅብረተሰቡ የሚያደርገውን ጥንቃቄ በማጠናከር ወረርሺኙን መከላከል እንደሚገባም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ በበኩላቸው ዓመቱ በተለይም ኮሮናን በመከላከልና የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በሌሎችም የጤና መስኮች ላይ ተመሳሳይ ሥራዎችን በመስራት ስኬቶች የተመዘገቡ መሆኑን አንስተው ይህም በአዲሱ ዓመት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።