በቂ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት አቅርቦት በመኖሩ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ አሳይቷል - ኢዜአ አማርኛ
በቂ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት አቅርቦት በመኖሩ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ አሳይቷል
ጳጉሜን 05/2012(ኢዜአ) የበአል ገበያው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ከፍተኛ አቅርቦት በመኖሩ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ ማሳየቱን በላምበረት የአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ ለአዲስ አመት የበአል ፍጆታ ምርቶች ለመግዛት የመጡ ሸማቾችና ሻጮች ተናገሩ፡፡
ቀደም ባሉ ጊዜያት የነበረው በተለይም ለበአል ፍጆታ የሚውሉ የቀይና ነጭ ሽንኩርት ዋጋ ከ10-20 ብር ቅናሽ ቢያሳይም እንደ አቅርቦቱ ከዚህም በላይ መቀነስ እንደነበረበት ኢዜአ የበአል ገበያ ተዘዋውሮ ያናገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመዋል፡፡
ለበአል ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ገበያ ላይ በብዛት መግባታቸውና ካለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱን የነገሩን በላምበረት ሲገበያዩ ያገኘናቸው አስተያየት ሰጪ ወ/ሮ በዳቱ ኦልጅራ ናቸው፡፡
ሽንኩርት አዲስ ምርት በመሆኑ እርጥብ ቢሆንም በብዛት ገበያ ላይ አቅርቦት መኖሩና ቅናሽ ማሳየቱ መልካም መሆኑን ገልፀው፤ ከ20 እስከ 24 ብር መሸጡ ግን አግባብ አይደለም ይላሉ።
ማህበረሰቡ በአሉን በጤና ለማሳለፍ ቅጣትን በመፍራት ሳይሆን ለራሱ እና ለቤተሰቡ ደህንነት ሲባልና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የድርሻው ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።
በላምበረት አትክልት በመሸጥ ላይ የነበሩት አቶ አሸናፊ በላይ ለበአል ፍጆታ የሚውሉ የአትክልት ምርቶች በብዛት መግባታቸው ይናገራሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት በ30 እና በ40 ብር ሲሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ከ10-20 ብር ቅናሽ በማሳየት ከ20-23 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑ ነግረውናል፡፡
በተመሳሳይ ቀደም ሲል የአንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት ዋጋ ከ150-200 ብር ድረስ ሲሸጥ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ግን በኪሎ ከ80-100 ብር እየሸጠ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡
በድንች፣ቃርያ ፣ቲማቲም፣ሙዝ፣ሎሚ፣ ካሮት፣ቅጠላቅጠሎችና የመሳሰሉት ምርቶችም በተመሳሳይ የበአል መቃረብን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ምርት ወደ ገበያ በመግባቱ ቅናሽ አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
በተለይም በዚህ ገበያ የኮቪድ-19 ወረርሽኙ ጠፍቷል የተባለ ነው የሚመስለው ያሉት አቶ አሸናፊ፤ ማስክ የሚጠቀምና ርቀቱን ጠብቆ የሚገበያይ ሰው ቁጥሩ ትንሽ ነው ይላሉ፡፡
በመንግስት ደረጃ ተቀምጦ የነበሩ ክልከላዎች መነሳቱ የነበረው መዘናጋት ተባብሶ እንዲቀጥል አድርጎታል ብለዋል፡፡
ስሙን መጥቀስ ያልፈለገው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ከገበያ የበአል አስቤዛ ገዝተው ሲወጡ ያናገርናቸው፤ የምርት አቅርቦቱና መጠነኛ የዋጋ ቅናሹ መልካም ቢሆንም ከአቅርቦቱ አንፃር አሁንም ዋጋው ደሃው የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ አይደለም ብለዋል፡፡
ነጋዴው በበአል ወቅት ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም ማህበረሰቡ ምንም አማራጭ የለውም በሚል የሚያደርገው የዋጋ ጭማሪ በመተው ችግሮችን አብሮ ተጋግዞና ተዛዝኖ ማለፍ እንደሚገባም ይመክራሉ።
ማህበረቡም ነገን ራሱንና ቤተሰቡን በጤና ለማቆየት ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች የሚነገረው መልእክት ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
በርከት ያሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ሲሸጥ ያገኘናቸው ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ወንድማገኝ ሞገስ በበኩላቸው፤ አቅርቦት ላይ ምንም አይነት ችግር እንደሌለና ነጋዴውም በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ላይ እንደሆነ ነግረውናል፡፡
ከአሁን በፊት የምርት እጥረት ሰለነበረ በአትክልትና ፍራፍሮዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ምርቶችም ቢሆን ጭማሪ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን በቂ ምርት በመግባቱ የዋጋ ቅናሽ መስተዋሉን ጠቅሷል፡፡
በግብይት ወቅት የሚኖረው ንክኪ ለመቀነስ ራቅ ብሎ እንደሚያስተናግድና ብር ሲቀበልም ሆነ መልስ ሲሰጥ በሳኒታይዘር አፅድቶ እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ ወንድማገኝ፤ በሌሎች ነጋዴዎችም ሆነ ሸማቾች የሚስተዋለው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት መክሯል፡፡