''የአዲስ አበባ ውበት ለኛም ተጨማሪ ገቢ ማግኛችን ነው'' - የተለያዩ ሆቴሎች - ኢዜአ አማርኛ
''የአዲስ አበባ ውበት ለኛም ተጨማሪ ገቢ ማግኛችን ነው'' - የተለያዩ ሆቴሎች

አዲስ አበባ፣ጳጉሜ 5/2012 (ኢዜአ) አዲስ አበባ ከተማ እያማረችና እያበበች መሄዷ በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች ገቢያቸው እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን በመዲናዋ የሚገኙ ሆቴሎች ገለጹ።
ሳሬም፣ ግራንድ ኤሊያና እና ጁፒተር ዓለም ዓቀፍ ሆቴሎች በአዲስ አበባ መንገድ አካፋይ ላይ ችግኝ ተክለው የጎዳና ተዳዳሪዎችን መግበዋል።
የሦስቱ ሆቴሎች ሠራተኞች በራሳቸው ተነሳሽነት በመዲናዋ ቸርችል ጎዳና መንገድ አካፋይ ላይ ዛሬ ችግኝ የተከሉት።
የግራንድ ኤሊያና ሆቴልና ኮንፍረንስ ማዕከል የገበያና ሽያጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘበነ ኩራባቸው እንዳሉት ሆቴሉ መሰል ስራዎችን በየዓመቱ ሲያደርግ መቆየቱን ይገልጻሉ።
ተግባሩ የሕሊና እርካታን ከመስጠቱ ባለፈ አዲስ አበባ ጽዱና ውብ እንድትሆን የሚያስችላት መሆኗንም ነው የተናገሩት።
ይህም የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ ሆቴሎች ገቢያቸው እንዲጨምር የሚያደርግ ሲሆን ለከተማዋም ተጨማሪ ገቢ ማግኛ መሆኑን አቶ ዘበነ ጠቅሰዋል።
ሌሎች የከተማዋ ሆቴሎች ይህን በጎ ተግባር ቢያጠናክሩ የተሻለ መሆኑንም አቶ ዘበነ ተናግረዋል።
የሳሬም ዓለም አቀፍ ሆቴል የገቢያ ባለሙያ ወይዘሪት እየሩሳሌም ዳዊት የከተማ ውበት ለሆቴሎች መሰረት መሆኑን ገልጻለች።
"የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩ ከምንም በላይ ለትውልድ የሚተላለፍ ውብ ከተማ መመስረት ያስችላል" ነው ያለችው።
ሌላው የጁፒተር ዓለም ዓቀፍ ሆቴል የሰው ሀብት ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ጥበቡ በበኩላቸው "የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት የሚደነቅ ነው" ብለዋል።
የአዲስ አበባ ውበት እየጨመረ ሲመጣ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ የሆነው የቱሪዝሙ ዘርፍ እንዲቀላጠፍ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ አበባን የማስዋብ ሥራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስጀማሪነት በስፋት እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።
በዛሬው ዕለትም የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የወዳጅነት አደባባይ ተመርቋል።