የትራምፕ ውሳኔ ከኢትዮጵያ ይልቅ ግብጽን ይጎዳል - ኢዜአ አማርኛ
የትራምፕ ውሳኔ ከኢትዮጵያ ይልቅ ግብጽን ይጎዳል
ጳጋሜን 5/2012(ኢዜአ) የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኢትዮጵያ ሲያደርጉት የነበረውን እርዳታ እንዲታገድ ማድረጋቸው ይበልጥ ግብጽን ይጎዳታል ሲል እንግሊዝ ውስጥ የሚታተመው አል አራቢ የተባለው ድረገጽ አስነበበ።
ዶናልድ ትራምፕን የከበቧቸው የሪፐብሉካን ፓርቲ ሰዎች ሁለቱንም ሃገራት በገለልተኝነት እንዲታዘቡ ከማድረግ ይልቅ ፕሬዝዳንቱ ለግብጽ ድጋፋቸውን እንዲያሳዩ ማድረጋቸውን ያነሳው ድረገፁ ግብጽ የስምምነት ሰነዱን ብትቀበለውም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የአሜሪካን አቋም ባለመቀበላቸው በዋሽንግተን ሲካሄድ የነበረው ድርድር ሊሳካ አልቻለም ብሏል።
ግብጽ ጉዳዩን ከሚገባው በላይ በማጦዝ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ ያደረገችው ጥረት ሊሳካ ባይችልም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የምተገኘው እርዳታ እንዲታገድ ማስደረግ ችላለች ያለው ጽሁፉ የትራምፕ ውሳኔ ግብጽን ከመጥቀም ይልቅ ይበልጥ የሚጎዳትና ኢትዮጵያንም ከድርድሩ የሚያርቃት መሆኑ ሊታሰብበት ይገባ እንደነበር ገልጿል።
ትራምፕ ለሚያስቡት የመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ስኬት ግብጽን ብቻ ነጥለው ድጋፍ ማድረጋቸው ወትሮውንም ግድቡ ሲገነባ ዝምታን መርጠው የነበሩት ቻይናና ሩሲያን ይበልጥ ወደ ኢትዮጵያ እንዲጠጉ መልካም አጋጣሚዎችን የፈጠረ ነው ያለው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የቀድሞ ባለስልጣናትና የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ኢትዮጵያን በመደገፍ ለትራምፕ ውሳኔ ተቃውሞዋቸውን ማሰማታቸው ለግብጽ ባለስልጣናት የሚያስተላልፈው መልእክት ከባድ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብሎታል።
ስመጥር የዴሞክራቲክ ኮንግረስ አባላት ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የበላይ ማይክ ፖምፒዮ በጻፉት ደብዳቤ በጸረ ሽብር ትብብር በምስራቅ አፍሪካ ዋነኛ የአሜሪካ አጋር በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ የተደረገው ድጋፍ የማገድ ውሳኔ የፕሬዝዳንቱን አፍቃሬ-ግብጽ መሆን ያመለክታል ማለታቸውን ያስታውሳል።
ውሳኔው ለግብጽም ሆነ ከጆ ባይደን ጋር ለሚወዳደሩት ትራምፕ ትልቅ ሽንፈት ከመሆኑም በላይ በርካታ የአሜሪካ ተቋማት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ እያደረገ ነው ብሏል።
ድረገጹ ስማቸውን ካልገለጹ የግብጽ ባለስልጣናት ሰማሁት ባለው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ግድቡን በሚመለከት በቀጣይ ጊዜያት የምታደርጋቸውን ውይይቶችና ድርድሮች ለማስቀጠል የአሜሪካን ከታዛቢነት ገለል መደረግ እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ጉዳዩን ይበልጥ ልታወሳስበው እንደምትችል ስጋቱን ገልጿል።
እንደ ድረገጹ ምንጮች ማብራሪያ ከሆነ ቀድሞውኑ የግብጽን ጥቅም ለማስጠበቅ የ2.9 ቢሊየን ዶላር ብድር ከአይ ኤም ኤፍ ማስከልከልና ለኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መስጠትና በኢትዮጵያ የሚሰሩ የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ማእቀብ እስከመጣል የሚደርስ እርምጃዎችን ኢትዮጵያ ላይ ማሳረፍ ታስቦ የነበረ ነው።
ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከትራምፕና ከፖምፒዮ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ለመደራደር ዝግጁ በመሆናቸው እቅዶቹ ሳይተገበሩ መቆየታቸውን ተናግሯል።
አፍሪካ ውስጥ ቻይናን ማየት የማይፈልጉ የአሜሪካ ፖለቲከኞች አሜሪካ አፍሪካ ላይ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በአንድ በኩል እርዳታ ክልከላን ፣ማእቀብንና የመሳሰሉትን ሲያስቀድሙ በተቃራኒው ሌሎች ደግሞ አፍሪካ ላይ ሃብት በማፍሰስና የልማት እገዛዎችን በማድረግ የቻይናን ስር መስደድ ማስቆም እንደሚቻል ሙግቶች መኖራቸውን አንስቶ ድርድሩ ቀድሞውኑ ለግድቡ ምንም አስተዋጽኦ የሌላት አሜሪካን ዋጋ አሳጥቷታል ብሏል።
አሁን ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ጀርመን ኢትዮጵያን በመደገፍና ግድቡ ግብጽ እንደማይጎዳ በማመን በግንባታው ውስጥ በቀጥታ እየተሳተፉ ያሉት ቀጣይ ሊያገኟቸው የሚችሏቸውን የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የልማት ጥቅሞች ታሳቢ በማደረግ ነው ያለው ድረገጹ።
ኢትዮጵያ የተራዘመ የድርድር ሂደት በመከተል ያለምንም ስምምነት ግድቡን ማጠናቀቅና መሙላት እንደምትፈልግ አቤቱታውን አሰምቷል።