የጠቅላይ ሚኒስትሩን የልማት ፕሮጀክቶች እንደሚደግፉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የልማት ፕሮጀክቶች እንደሚደግፉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ
አሶሳ፣ ጷጉሜን 5/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀገርን ከድህነት ለማላቀቅ የሚካሄዷቸውን የልማት ፕሮጀክቶች በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በአሶሳ ከተማ አስተያየታቸወን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አስመልከተው አስተያየተቻውን ከሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ነስሮ ጣሃ ለኢዜአ እንደተናገረው የዶክተር ዐቢይ ማብራሪያ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ብዥታዎችን ያጠራ ነው።
በትግራይ እየተካሄደ በሚገኘው ክልላዊ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የያዙት አቋም ትክክለኛና የሚደገፍ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠናክር ነው ብሏል።
ዓለም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽን እየተቸገረ ባለበት በአሁኑ ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን በሚቃረን መልኩ በትግራይ የሚካሄድ ምርጫ ተገቢ እንዳልሆነ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ትግራይ የኢትዮጵያ አንዷ አካል ነች ያለው ወጣቱ በሕግና በአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚመራ ሀገር ሕጎች ሊተገበሩ እንደሚገባም ተናግሯል።
ሕዝብን ከሕዝብ ለመነጠል የሚደረግ ጥረት አላስፈላጊ መሆኑን ጠቅሶ ፓርቲና ሕዝብ የተለያዩ እንደሆኑም አስረድቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገርን ለመለወጥ ያላቸው ራዕይ የሚደገፍና ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ሃሩን መንስሩ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።
ከለውጡ በፊት ለሕዳሴው ግድብ ሕዝቡ ባደረገው ርብርብ ልክ መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ እንዳልሰራ ጠቅሰው ፕሮጀክቱን ከጥፋት ለማዳን በተወሰደው እርምጃ የተገኘው ውጤት ከለውጥ መሪ የመጣ እንደሆነ ገልጸዋል።
አቶ ዘውዱ ዛምባሎ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ገበታ ለሸገርና ለሀገር ፕሮጀክቶች በሀገር ባለሙያና ገንዘብ ብቻ እየተሰራና ውጤታማ እየሆነም መምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያስመሰግናቸዋል ብለዋል።
ለጥሩ ነገር ያልተፈጠረ አእምሮ ዘወትር ያለምክንያት ይተቻል ያሉት አስተያየት ሰጪው ፕሮጀክቶቹ በተለይ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ መረዳታቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የያዙትን ሀገር የማልማት ጥረት እንደሚሳካ እምነት እንዳላቸው የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ የሕዳሴውን ግድብ ጨምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት እንዲለማ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።