ዓመቱ በኢንቨስትመንትና በንግድ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለበት ነው--- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ዓመቱ በኢንቨስትመንትና በንግድ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለበት ነው--- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ጷጉሜን 5/2012 (ኢዜአ) የተጠናቀቀው የ2012 ዓ.ም በኢንቨስትመንት እና በንግድ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለበት ዓመት እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በአዲሱ ዓመት ከኢንቨስትመንትና ንግድ ዘርፎች በተጨማሪ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በቱሪዝም ዘርፎች ውጤት ለማምጣት ዝግጅት መደረጉም ተጠቁሟል።
አዲስ ዓመትን አስመልክቶ መልካም ምኞታቸውን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ''የተገባደደው 2012 ዓ.ም በፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል'' ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በቱሪዝምና በቴክኖሎጂ ሽግግር አንጻር የሚሰራቸውን የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ለማሳካት ጥረት ማድረጉን ጠቁመዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ሁሉንም አካል በተለያየ መንገድ በመንካት አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስታውሰዋል።
በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ የተሻለ ውጤት እንደተመዘገበ ወይዘሮ ጽዮን ተናግረዋል።
የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የጀመረበት ጊዜ ቅርብ በመሆኑ የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ገልጸው፤ በኢንቨስትመንት ላይ ከሚሰሩ ተቋማት፣ ከኤምባሲዎችና ከኢንቨስተሮች ጋር በመነጋገር ማነቆዎችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስና በንግድ ላይ ያሳረፈው ጫና የበረታ ቢሆንም በኢትዮጵያ የወጭ ንግድ አፈጻጸም መልካም እንደነበረ ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውሰዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የነበረውን ብቃት ተጠቅሞ የሠራው ሥራ የሚደነቅ እንደሆነ አመልክተዋል።
ከተለያዩ ማኅበራት ጋር በመነጋገር የምርት መዳረሻ ትኩረትን በመለየት የተሰራው ሥራና የአገሪቱ ዲፕሎማቶች ጥረት ለወጭ ንግዱ ስኬት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
በ2012 ዓ.ም በቴክኖሎጂ ሽግግር የተወሰነ መዳከም እንደነበረ የተናገሩት ወይዘሮ ጽዮን፤ ''የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በስፋት ለመንቀሳቀስ አላስቻለም'' ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን የመለየትና የመምረጥ ሥራ መሥራታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በቀጣይ ዲፕሎማቶች የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ የመለየት ተግባር መከናወኑን ጠቁመዋል።
''በቴክኖሎጂ ወደኋላ መቅረትን ወደ ዕድል መቀየር የምንችለውና ቴክኖሎጂዎችን ለእኛ አገር ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው የሚለውን መረዳት ላይ ተግባብተናል'' ብለዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ በ2013 ዓ.ም በስፋት ለመሥራት የሚያስችል መሠረት መጣሉን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ 'ጤና ይስጥልኝ' የሚል ዘመቻ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።