ቀጥታ፡

ለውጡን ማስቀጠል ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ

አዳማ፣ ጳጉሜ 05/2012 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር የመጣውን ለውጥ ማስቀጠል በሀገሪቱ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አስተያያት ሰጪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምሁራንና የአካባቢው ነዋሪዎች  እንዳሉት ከለውጡ ወዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ስኬቶች እንደተገኙ ዶክተር አብይ በተጨባጭ አሳይተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል ዲን ዶክተር ዓለሙ ጉንፋ እንደገለጹት በሀገሪቱ ብሎም በቀጠናው መረጋጋት እንዲመጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለዓለም የሰላም ኖቬል ሽልማት እንዲበቁ አስችሏቸዋል።

እየታየ ካለው ከፖለቲካ ስኬቱ ባለፈ ግንባታው ቆሞ የነበረው የህዳሴው ግድብ በእሳቸው ቁርጠኝነት  በማስቀጠል ብሔራዊ ኩራታችንን ማስጠበቅ የቻልንበት ሌላው ማሳያ ነው ብለዋል።

ይህ ስኬት የእሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ህዝቦች ትልቅ ድል መሆኑን የገለጹት ዶከተር ዓለሙ፤ በቃለ ምልልሳቸውም ይህንን እውነታና የኢትዮጵያ  ነበራዊ ሁኔታ በተጨባጭ እንደተመላከተ መረዳታቸውን ገልጸዋል።


በትግራይ ክልል ብቻ ምርጫ መካሔዱ የኢኮኖሚ ብክነትና ትርጉም የሌለው ከንቱ ድካም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት በምክንያት እንደሆነ መገንዘባቸውንም ጠቅሰዋል።

ለትግራይ ህዝብ አሁን የሚያስፈልገው የፖለቲካ ምርጫ ሳይሆን ከኮሮና በመታደግ ውሃና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክል እንደሆነ አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለትግራይ ህዝብ ያላቸውን ትልቅ ክብርና ወገንተኝነትን ያረጋገጠ ቃለ ምልልስ ነው ብለዋል።

" የፖሊቲካ ምህዳሩ የጠበበ እንዳልሆነ  ማሳያው  ሁሉም ወገኖች የሀገር ጉዳይ እንደሚመለከታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመኑና የገቡትን ቃል ያከበሩ ናቸው" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የውሃ ምህንዲስና መምህር ዶክተር ኬይረዲን ተማም ናቸው።

በዚህም ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶም ሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች በሀገር ጉዳይ ላይ እንዲመክሩ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱን የሚያረጋግጥ  እንደሆነ ጠቅሰዋል።


ቀጣይ በሚደረገው ሃገራዊ ምርጫ የህዝቡ ውሳኔ የሚረጋገጥ ቢሆንም አሁን ያለው የለውጡ አመራርና መንግስታቸው ትልቅ ህዝባዊ ድጋፍ ያላቸው መሆኑን መካድ አይቻልም  ብለዋል።

የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት፣ የአንድነት ፓርክ፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፣የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብርና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ላይ ህዝቡ እያደረገ ያለው ርብርብ መንግስታዊ ድጋፍና ተቀባይነት መኖሩን ማሳያ እንደሆኑ ዶክተር ኬይረዲን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግስትና መሪ ድርጅታቸው ህዝባዊ ድጋፍ ያላቸው መሆኑን የገለጹበት ማሳያ ትክክል መሆኑን  ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዎቹ የመጣውን ለውጥ ማስቀጠል በሀገሪቱ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።


ህዝቡ ጥሩውንና መጥፎውን በመለየት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሂደት እየደገፈ ያለው በምክንያት ነው ያሉት ደግሞ የአዳማ ከተማ ቦኩ ሸነን ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደጀነ ንጉሴ ናቸው።

ሀገሪቱ የተሻለ የልማት ስኬቶችን እያስመዘገበች ከመሆኑም ባለፈ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷና ተሰሚነቷ ከፍ ያለው በእሳቸው አመራር መሆኑን ተናግረዋል።


የዚህ ማሳያ የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌ በስኬት መጠናቀቅ፣  የጎረቤት ሃገራት የፖለቲካ አለመግባባትን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመፍታት ያመጡትን ለውጥ ጠቅሰዋል።


ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የተደረጉ ጥረቶች በመንግስት በሳል  አመራር  መግታት መቻሉን ሌለው አስተያየት ሰጪ  አቶ አንቷን ቱና ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም