ቀጥታ፡

የፋይናንስ ተቋማት ለ''ገበታ ለሀገር'' ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጷጉሜን 5/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ለ''ገበታ ለሀገር'' ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገበታ ለአገር ፕሮጀክትን አስመልክቶ ከፋይናንስ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ውይይት አድርጓል።

ፕሮጀክቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  ዐቢይ አህመድ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ፕሮጀክቱ በጎርጎራ፣ በወንጪና ኮይሻ እንደሚለሙም ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለፕሮጀክቱ 30 ሚሊዮን ብር ለመስጠት በቦርዱ አማካኝነት መወሰኑን ገልጿል።

ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎች ፕሮጀክቱን በፋይናንስ በሚደግፉበት ሁኔታና የፕሮጀክቱ የፋይናንስ አጠቃቀምና ግልጽነት ዙሪያ ሀሳብና ጥያቄ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ፕሮጀክቱ በግልጽ የፋይናንስ ሥርዓት የሚመራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ አገርን ከማሳደግ አኳያ ያላቸው ሚና ወሳኝ እንደሆነና ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል።

የፋይናንስ ዘርፉም ለፕሮጀክቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ባንኩ ለተቋማቱ የድጋፍ ጥያቄ ደብዳቤ እንደሚልክና ሁሉም በቦርዳቸው ተወያይተው እስከ መስከረም 2013 መጨረሻ እንዲያሳውቁ አሳስበዋል።

በመንግሥት በኩል ከፋይናንስ ተቋማት የሚደረገውን ድጋፍ የሚያስተባበር ኮሚቴ መቋቋሙንና በሚቀጥለው ሣምንት ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጋር ይወያያል ብለዋል።

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ቢያንስ ሦስት ቢሊዮን ብር ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

“ገበታ ለሀገር” አዲስ አበባ ከተማ የተካሄዱትን የአንድነት፣ የሸገርና የእንጦጦ ፕሮጀክቶችን በሦስት ክልሎች ለማስፋት ገቢ ለማሰባሰብ የተዘጋጀ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም