ኢትዮጵያዊያን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የማይናወጥ አቋም በመያዝ ታሪክ መስራት ይችላሉ -ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የማይናወጥ አቋም በመያዝ ታሪክ መስራት ይችላሉ -ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የማይናወጥ አቋም በመያዝ ታሪክ መስራት ይችላሉ ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
ፕሬዝዳንቷ በሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ የምረቃ ስነ-ስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነቡት ፓርኮች በትብብር ለውጥ ማምጣት እንደምንችል ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የህዝብ መዝናኛና የተለያዩ ሁነቶች የሚከወኑበት አስደናቂ ፓርኮችን ማግኘቷ ደረጃዋን ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።
ሸገር ፓርክን ጨምሮ ሌሎች በከተማዋ የተገነቡ ፓርኮች የከተማዋን እንዲሁም የአገሪቱን ገጽታ በመለወጥ ትልቅ አስተዋጾ እንዳላቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በንግግራቸው" ተስማምተንና ተግባብተን ያለንን አቅም አሰባስበን በጋራ ፍላጎታችን ላይ ስንዘምት ታሪክ መስራት እንደምንችል ህያው ምስክር ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ያላቸው ሃብትና ውበት አንድነትንና የተሻለ ህይወትን አጣምሮ ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህንን ለማድረግ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የማይናወጥ አቋም በጽናት መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ።
አሁን ከተገነቡት ከፓርኮች ልምድ በመውሰድ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ክፍት ቦታዎች መጠነኛ ፓርኮችን መስራት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት ከተማዋን ለማስዋብ ሊሰሩበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከተማዋን ከማስዋብ ጎን ለጎን ዋና ትኩረት ለሆነው የልማትና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በሚደረጉ ጥረቶች ላይ መረባረብ ይገባልም ብለዋል።
ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረና መተዳደሪያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሸገር ፓርክ ብዙ የህዝብ መዝኛ የሏትም ተብላ ለምትታማው አዲስ አበባ በሌላ ከፍታ የሚያስቀምጣት መሆኑንም ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ለአዲሱ አመት የመልካም ምኞት መግለጫቸውንም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አስተላልፈዋል።