ቀጥታ፡

አማራጭ ኃይል ተጠቃሚ በመሆናቸው ሕይወታቸው መሻሻሉን የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ

ደብረ ብርሃን ሐምሌ 6/2010 የባዮ ጋዝ ማብለያ ገንብተው አማራጭ ኃይል ተጠቃሚ በመሆናቸው ሕይወታቸው መሻሻሉን በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ። አቅም የሌላቸው አርሶ አደሮችን በባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግም መንግስት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የዞኑ ውሃ መስኖና ኢነርጂ መምሪያ አስታውቋል። በዞኑ የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አለሙ ይታገሱ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ልኬቱ ስድስት ሜትር ኩብ የሆነ የባዮ ጋዝ ማብላያ ገንብተው ለአገልግሎት አብቅተዋል። ለግንባታው ከራሳቸው ጉልበት በተጨማሪ ከመንግስት በድጋፍ ያገንኙትን 7ሺህ 500 ብር ገንዘብ ለስራው ማዋላቸውን ተናግረዋል። “አማራጭ ኃይል በመጠቀሜ የማገዶ እንጨት ለመግዛት አወጣው የነበረውን ገንዘብ ማዳን ከመቻሌም ባለፈ ማገዶ ለማጓጓዝ የወጣውን ጉልበትና ጊዜ ቆጥቤያለሁ” ብለዋል። በባሶና ወረና ወረዳ ባቂሎ ቀበሌ ሴት አርሶ አደር እታገኘሁ ማስረሻ በበኩላቸው 16 ሚትርክ ኩብ ስፋት ያለው የባዮ ጋዝ ማብላያ በመገንባት መጠቀማቸውን ተናግረዋል። የባዮ ጋዝ ተረፈ ምርቱን በመስኖ ልማት ለሚያመርቱት ጎመን፣ ሰላጣና ሌሎች የጓሮ አትክልቶች ማዳበሪያነት እያዋሉት መሆናቸውን ገልጸው ይህም ተጠቃሚነታቸውን ከጊዜ ወደጊዜ እያሳደገው መሆኑን አስረድተዋል። የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰለሞን ሽፈራው አማራጭ ኃይል በመጠቀማቸው በኩራዝና እንጨት ጭስ ምክንያት በዓይንና በመተንፈሻ አካላቸው ላይ ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት መከላከል እንዳስቻላቸው አስረድተዋል። በተጨማሪም ለጋዝ፣ ለባትሪ ድንጋይና ለመሳሰሉት ያወጡት የነበረውን 4 ሺህ ብር ዓመታዊ ወጪ እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል። አርሶ አደሮቹ ያገኙትን ጥቅም ለሌሎች በማስተማራቸው በአሁኑ ወቅት ጎረቤቶቻቸው የባዮ ጋዝ ማብላያ አስገንብተው መጠቀም መጀመራቸውን ተናግረዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መስኖና ኢነርጂ መምሪያ በበኩሉ በተጠናቀቀው የ2010 በጀት ዓመት በዞኑ 37 ሺህ 482 አርሶ አደሮች የባዮ ጋዝ ማብለያ ቴክኖሎጂ ገንብተው ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቋል። በመምሪያው የአማራጭ ኢነርጂ ቡድን መሪ አቶ ክብሩይስፋ ዲበኩሉ እንዳሉት የባዮ ጋዝ ማብላያ ተጠቃሚዎች አቅም የሌላቸው የዞኑ አርሶ አደሮች ሲሆኑ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ዘንድሮ የባዮ ጋዝ አማራጭ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ2 ሺህ መቀነሱን ጠቁመው፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ግብዓት ማቅረብ አለመቻሉ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። በዞኑ በ2010 በጀት ዓመት ለማገዶ ይውል የነበረ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኪሎ ግራም እንጨት በማስቀረት በተፈጥሮ ደን ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት በዞኑ 145 ሺህ 585 አርሶ አደሮች ባዮ ጋዝ ገንብተው በመጠቀም ላይ መሆናቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም