በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራት በሚጠግኑ አዲስ አስተሳሰቦች ላይ በትኩረት ይሰራል ... ብልጽግና ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራት በሚጠግኑ አዲስ አስተሳሰቦች ላይ በትኩረት ይሰራል ... ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2012(ኢዜአ) በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራት በመጠገን ለትውልድ የሚተርፍ ለውጥ ለማምጣት በአዲስ አስተሳሰቦች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ብልጽግና ፓርቲ ገለፀ።
አገራዊ ለውጡን መሬት ለማውረድ ለሚያከናውነው ተግባርም ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ኢትዮጵያዊያን የበኩላቸውን አንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።
የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኅላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አዲሱን አመት በማስመልክት ከኢዜአ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።
በነበራቸው ቆይታም አገራዊ ለውጡ ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚዊና ማህበራዊ ጥያቄዎችን አጀንዳዎች ያደረገ ህዝብ አበይት ፍላጎቶች እንዲመጡ ግፊት የነበረበት ነው ብለዋል።
የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች፣ ሕብረ ብሔራዊነት፣ ህዝባዊ ተጠቃሚነትና ሌሎች በህዝብ ግፊት የተነሱ አንገብጋቢ አጀንዳዎች ምላሽ እንዲያገኙና ለውጥ ፍሬያማ እንዲሆን ግን የለውጥ መሪ ያሻው ነበር ብለዋል።
በዚህም በለውጥ መሪነት ከቆሞ ቀርነት ወደ የተራማጅነት አስተሳሰብ በማንገብ ለውጡ ፍሬ እንዲያፈራ ብልጽግና ፓርቲ ሃላፊነቱን ስለመወጣቱ አንስተዋል።
ለውጡ ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ እንዲራመድ፣ የራሱ አሰራር፣ ደንብና ህግ ኖሮት፣ ፍኖተ ካርታ በማበጀት ለውጡን ሊቀለብሱ ከሚሞክሩ ሃይሎች ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።
እንደ ዶክተር ቢቂላ ገለፃ ለውጡ በህዝብ ግፊት ይምጣ እንጂ የለውጡ ስኬት ግን በፓርቲው ለዓመታት ያልተሰሩትን በማረም፣ መልካም ወረቶችን በማስቀጠል በተራማጅነት ከውስጥ የመጣ ነው።
አገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያዊያን በውይይት ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ያሳዩበት፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተስፋ የተጣለበት፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዕውቅና የቸረውና አገርን ከብተና የታደገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሁለት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የለውጥ ሂደት ለሰው ልጆች ክብር የሚሰጥ፣ ከፖለቲካ አስተሳሰብ ድርቅ ያወጣ፣ ኢትዮጵያዊያንን በወድማማችነት ያሰባሰበ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስብራትን የጠገነ ነውም ብለዋል።
ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ የነበረው ለውጥ በተለይ ፓርቲው በአገር አቀፍ ደረጃ እንደ ብልጽግና ከተዋቀረ በኋላ በአስተሳስብ የለውጥ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል።
በ2013 ዓ.ም ፓርቲው በኢትዮጵያ የነበረውን የፖለቲካ ስብራት ለመጠገን በአዲስ አስተሳስብ ለውጡ መሬት እንዲይዝ በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ ዘርፈ ብዙ ተግበራት እንደሚከናወን አንስተዋል።
በአዲሱ ዓመት የአስተሳሰብ ለውጥ ስራው በመንግስታዊና በፓርቲው መዋቅር የዕለት ከዕለት ተግባር ላይ እንዲውል የስራ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ይሰራል ብለዋል።
ፓርቲው በህግ የበላይነት፣ በህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በተግባር የሚተረጎም እውነተኛ ብልጽግና ለማምጣትና ሁለንተናዊ የህዝብ ፍላጎትን ለማሟላት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በአዲሱ ዓመት ለውጡ ተጠናከሮ እንዲቀጥል፣ በአገራዊ መግባባትና ለውጡ ህዝባዊ ይሁንታና ባለቤትነት አግኝቶ እንዲሄድም ይሰራል ብለዋል።
ፓርቲው በአዲሱ ዓመት ለማከወናውን ያቀዳቸው ተግባራት ዕውን ማድረግ እንዲችል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሃላፊነት ሲመጡ አገርን ለማሻገር ለሁሉም ወገኖች እንዳደረጉት ጥሪ፤ አሁንም ከምሁራን፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከኢትዮጵያ ተቆርቋሪ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል ዶክተር ቢቂላ።
ፓርቲው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ስብራት በመጠገን ወደ አገራዊ ብልጽግና ለመሸጋገር ለሚደረገው ጥረት ሁሉም ትብብርና እገዛ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር በሚደረጉ በውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ዙሪያ በማዕከላዊ መንግስት ብቻ የሚከወን እንደሆነም አረጋግጠዋል።
በዚህ ረገድ የክልል መንግስታት ጉዳያቸውን በፌዴራል መንግስት ያስፈጽማሉ እንጂ በራሳቸው በማንኛውም ጉዳይ ከውጭ አገራት ጋር ግንኙነት ማድረግ የማይችሉ መሆኑም ይታወቃል ነው ያሉት።
ከህግ ውጭ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ላይ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው፣ ከዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮም የሚጻረር ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።