ቀጥታ፡

ተቋማት የሚገነቡበትን መሰረት መልሰን ማረም ካልቻልን አገር አይገነባም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 4/2012 ( ኢዜአ) ''ተቋማት የሚገነቡበትን መሰረት መልሰን ማረም ካልቻልን አገር አይገነባም'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አመትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸው እንደተናገሩት፤ አገር የምትቆምበት ምሰሶ በእኩል ደረጃ ካልተገነባ አገረ ግንባታው የተሟላ ሊሆን አይችልም።

ኢትዮጵያ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ፣ ብዙ ቋንቋ፣ ብሔር፣ ልምምድና ዕምነት ያለበት ትልቅ ማዕቀፍ መሆኗን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የቆመችበት አራት ዋነኛ ምሰሶዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

ከአራቱ ምሶሶዎች ሶስቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንና አራተኛው ምሰሶ የራሱ ውስንነት ቢኖረውም ከሞላ ጎደል የተሻለ እንቅስቃሴ እንደነበረው አመልክተዋል።

በአንደኛው ምሰሶ ብቻ አገር የማይቆም መሆኑን በመገንዘብ ሁሉንም ምሰሶ ማጠናከር ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአገሪቱ ለውጡ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት አመታት በተጎዱት ምሰሶዎች ላይ በስፋት መሰራቱን አመልክተዋል።

''አንደኛው ኢትዮጵያን እንደ አገር የሚያቆማት ምሰሶ 'አልትራስትራክቸር' የሚባለው ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እምነት፣ ባህልና ትውፊት በዚህ መዋቅር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

''እነዚህ ጉዳዮች እየጠፉ ከሄዱ አንደኛው ምሰሶ ይናዳል'' ብለዋል።

ለምሳሌ ኦርቶዶክስን የሚያክል ለሺህ ዓመታት የቆየ ማንነት ያለው ትልቅ ተቋም የራሱ ትውፊት፣ ዶግማ መዋቅር የአሰራር ስርአት ያለው ተቋም በነበረው የስርዓት ችግር ምክንያት ለሁለት ተከፍሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

የሙስሊምና የፕሮቴስታንት እምነቶችም እንዲሁ ሚናቸውን እንዲያጡ ተደርገው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ኦርቶዶክስ፣ ሙስሊምና ፕሮቴስታንት ስለ አንድነት እና ወንድማማችነት እያስተማሩና እየሰበኩ አገር ሊበታተን እንደማይችል ጠቁመው፤ ''የእምነቱ መሰረታዊ መቆሚያ መሰብሰብ፣ ህብረትና አንድነት ነው'' ብለዋል፡፡

''ይህንን ወደ አንድ ማምጣት ዛሬ ላይ ቀሎ ይታያል ነገር ግን ብዙዎች የታሰሩበት፣ የተሰደዱበት፣ የተጎዱበት፣ እምነታቸውን ጥለው የወጡበት፣ ከእምነት አካባቢ የሸሹበትና መከራ ያዩበት ነው'' ብለዋል፡፡

''ድሮ ሙስሊሞች ክርስቲያን ጋር ክርስቲያኑም  ሙስሊሙ ጋር በአደራ ዕቃ ሲያስቀምጥ በወርም በሁለት ወርም ቢመጣ ያገኘዋል'' ሲሉ ገልጸዋል፡፡

''ኦርቶዶክስ፣ ሙስሊምና ፕሮቴስታንት ጠንክሮ ከቆመ ከዚህ ውጭ ያለው ሰው በቁጥር እዚህ ግባ የማይባል ስለሆነ መንግስት እንኳን ባይኖር በዚህ በማይታየው አስተሳሳሪ ገመድ የተነሳ አገር ትቀጥላለች'' ብለዋል፡፡

ይሄንን አስተሳሳሪ ገመድ በከፍተኛ ሁኔታ መንግስት ሲያዳክም እንደቆየም አስታውሰው፤ ይህንን ለመቀየርና ምሰሶውን ለማጠናከር ብዙ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

''ሁለተኛ ኢትዮጵያ የቆመችበት ምሰሶ ''ሱፐርስትራክቸር'' የምንለው ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የእሳቤ ትርክት እንደሆነ ገልጸዋል።

''ለምሳሌ አንተ ወገን ነህ አጋር ነህ የሚል ከፋፋይ ሃሳብ በዘርና በሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በመዋቅር ኢትዮጵያዊ ሆኖ የኢትዮጵያን ድንበር የሚጠብቁ አብዛኛው ዜጎች አንድ ቀን የዚህ አገር መሪ መሆን የማይመኙበት ሁኔታ በጣም ከፋፋይ ነው'' ብለዋል፡፡

ትርክቱ በተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ክፍፍል የሚፈጥር አደገኛ ትርክት እንደነበረ አስታውሰዋል።

ለአብነትም ባለሃብቱን ልማታዊ ኪራይ ሰብሳቢ በሚል የሚከፋፍል እንደነበር ገልጸዋል።

የለውጡ ሁሉ ቁንጮ በኢትዮጵያ መፃኢ ጊዜ ውስጥ ትርጉም ያለው አሻራ ጥሎ ከሚያልፍ የታሪክ ክስተት ውስጥ አንዱ የብልጽግና መፈጠር እንደሆነ የገለጹት ዶክተር አብይ፤ ''ብልጽግና ትርክቱ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ መግባባት፣ ወዳጅነት፣ ወንድማማችነት፣ መበልጸግና እና መለወጥ ነው'' ብለዋል።

''ይህ ትርክት በጊዜ ብዛት መፈቃቀር፣ መዋደድ፣ አብሮ መሆንና መተጋገዝን ባህል እያደረገ ሄዶ የምንፈልጋትን አገር ይፈጥራል'' ብለዋል።

''ሶስተኛው ምሰሶ ኢንትራስተራክቸር የሚባለው ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ምሰሶው ተቋማት የሚፈጠሩበት መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ ሰባት ተቋማትን ማንሳት እንደሚቻል አመልክተው፤ የሃገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የብሄራዊ ደህንነት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ)፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የአዲሰ አበባ ፖሊስ፣ የፋይናንሺያል ኢንተሊጀንስ፣ ዐቃቤ ህግ እነዚህ ሰባት ተቋማት አይነኬ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

''የፈለጉትን የሚያስሩ፣ የሚገርፉ፣ የሚያባርሩና አትወጣም አትገባም የሚሉ ተቋማት ነበሩ'' ብለዋል።

እነዚህን ተቋማት ኃላፊ ብቻ መቀያየር ሳይሆን እሳቤያቸውን የመቀየር ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

''አሁን ብዙዎቹ ተሳክቶ ስላዩት አቅልለው የሚያዩት ቢሆንም መከላከያና ደህንነት ወይም ኢንሳ ላይ በቀለለ መንገድ አሁን ያደረግነውን አይነት ለውጥ ማድረግ አይቻልም'' ብለዋል፡፡

በነዚህ ተቋማት ምክንያት ብዙ የሆነ ውንብድናና ኪሳራ በአገር ደረጃ መድረሱንም ጠቅሰዋል።

በኢኮኖሚውም በመንገድ፣ ቴሌ፣ አየር መንገድ፣ ሜቴክ፣ ስኳርና ባቡር ዘርፎች ላይ የተቋም ግንባታ ላይ በስፋት መሰራቱን ተናግረዋል።

''ለምሳሌ ኤልፓን ብንወስድ አጠቃላይ የኩባንያው 99 በመቶ ዕዳ ነው፣ ማንም አይገዛውም፣ አይፈልገውም'' ብለዋል፡፡

''ተቋማት የሚገነቡበትን መሰረት መልሰን ማረም ካልቻልን አገር አይገነባም'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ምሰሶዎቹን ለማጠናከር እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

አራቱ ምሰሶዎች በእኩል ደረጃ መገንባት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም