ቀጥታ፡

በአፋር ክልል ያለውን ሰላም በአዲሱ ዓመትም ለማጠናከር የህብረተሰቡ ደጋፍ እንዲቀጥል ተጠየቀ

ሰመራ ጳጉሜ 4/2012 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ያለውን ሰላም በአዲሱ ዓመትም ይበልጥ ለማጠናከር ህብረተሰቡ ከጸጥታው ኃይል ጋር በመተባበር ድጋፉን እንዲቀጥል ተጠየቀ። 

የሰላም ቀን  የሀገር መካላከያ፣ የክልሉ ጸጥታና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት ዛሬ  በሰመራ ከተማ  በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሃመድ አወል በወቅቱ እንደተናገሩት የአፋር ክልል ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ያለስጋት በእኩልነት በጋራ የሚኖሩበት የመልካም እሴት ባለቤት ነው።

በአጎረባች ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮችን በጋራ በመፍታት  የልማትና የህዝቦች አብሮነትን የማጠናከር ስራዎችን  ሲከናወኑ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

ክልሉ ያለውን ሰላምና የህዝቦች አብሮነት ለማጎልበት  ህብረተሰቡ  ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ሲያደረግ የቆየውን ትብብርና  ድጋፍ በአዲሱ ዓመትም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባል  የመቶ አለቃ አሸናፊ አበበ በበኩላቸው በክልሉ ያለው ሰላም የበለጠ ተጠንክሮ እንዲቀጥል ከክልሉ ጸጥታ ጋር ተቀራርበው በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 ህብረተሰቡም ለሰላሙ ያለውን አጋርነት የበለጠ ማጠናከር አለበት ብለዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ መዲና መሃመድ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት  በመሆኑ በክልሉ ያለው ጸጥታ  ተጠብቆ እንዲዘልቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች አዲሱ ዓመት ዜጎች በሰላም አብረው ተከባብረው የሚኖሩባትና  የለማች ሃገር እንድትሆን ያላቸውን መልካም ምኞት የገለጹ ሲሆን  በመጨረሻም የችግኝ ተከላና የጽዳት ስራ አከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም