በጤና ዘርፍ የሚሰሩ ሙያተኞች ክህሎት ለማሳደግ እየተሰራ ነው-ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በጤና ዘርፍ የሚሰሩ ሙያተኞች ክህሎት ለማሳደግ እየተሰራ ነው-ጤና ሚኒስቴር
አዳማ ጷጉሜ 04/2012(ኢዜአ) የኮሮና በሽታ ስርጭትን ለመግታት በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ ሙያተኞችን ክህሎት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ በጤና ዘርፍ ከተሰማሩት 11 የጤና ሙያ ማህበራት ጋር በመሆን በሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የጤና ኤክስቴሽኖች ጭምር ተደራሽ ያደረገ ስልጠናና የአቅም ግንባታ እገዛ ለመስጠት የሚያስችል ፕሮግራም ትናንት በአዳማ ከተማ በተዘጋጀ መድረክ ይፋ አድርጓል።
በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ እንደገለጹት የኮሮና በሽታ ስርጭትን ለመግታት በዘርፉ የሚሰሩ ሙያተኞችን ክህሎት ለማሳደግ ያስፈልጋል።
የበሽታው ስርጭት እየተስፋፋ የህብረተሰቡ መዘናጋት አሳሳቢ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በተለይም ሙያተኞቹ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች አያያዝና በሚደረጉ ጥንቃቄ ላይ በክህሎት ዝግጁ ሆነው የጤና ተቋማትን እንዲያግዙ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ የፅኑ ህሙማን መብዛት፣ በበሽታው በየዕለቱ የሚያዙና ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ቁልፍ ስራችን መሆን ያለበት ህብረተሰቡን ማንቃትና ሙያተኞችን በአቅምና ክህሎት ማዘጋጀት ነው ብለዋል።
የስልጠናው ዓላማም እስከ ጤና ኬላ ድረስ ያሉ የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎችን ማብቃትና ትምህርታዊ ግንዛቤን በሁሉም ደረጃ ለማጠናከር እንደሆነም ገልጸዋል።
በዚህም በሽታውን ለመግታት በፈቃደኝነት የሚንቀሳቀስ ከ10ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞችን ለማፍራት ነው፤ የጤና ሙያ ማህበራት ስልጠናውን በመምራት እንዲያግዙን ያስችላል ብለዋል።
በተለይም መጪው ጊዜ ህዝባዊ በዓላት የሚበዙበት ወቅት በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጭምር እንደሆነም አመልክተዋል።
በሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ሙያዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ የሰው ኃይል ለማዘጋጀት የሚሰጥ ስልጠና መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ሳሙኤል ናቸው።
የሙያ ማህበራቱ እስካሁን ድረስ ለኮሮና በሽታ መከላከል ሀብት ከማሰባሰብ ጀምሮ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ስልጠናው በሽታው አሁንም አሳሳቢ በመሆኑ ለመግታት በሚደረገው ጥረት በሙያቸው እንዲያግዙ ለማስቻል መሆኑን አስረድተዋል።
ስልጠናው ከትናንት ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል እንደሚቀጥል ተመልክቷል።