ቀጥታ፡

ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ዘመናዊ የላቦራቶሪ ማዕከል ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ ጳግሜ 4/2012 (ኢዜአ) ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ለምስራቅ አፍሪካ ጭምር አገልገሎት ሊሰጥ የሚችል ዘመናዊ የላቦራቶሪ ማዕከል ሊገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።

ግንባታው ከዓለም ባንክ በተገኘ የ150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚካሄድም ኢኒስቲትዩቱ ገልጿል።

የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በቅርቡ የሚጀመረውን የላቦራቶሪ ማዕከል ግንባታና በበጀት ዓመቱ የኮቪድ-19 ምርመራና የመከላከል ሥራዎችን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በአገሪቱ ሰፊ አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ የላቦራቶሪ ማዕከል ባለመኖሩ ኮቪድ-19 በተከሰተበት ወቅት    ምርመራ ለማድረግና ነባራዊ ሁኔታውን ለማወቅ አዳጋች ሆኖ እንደነበር አስታውሰዋል።

በወቅቱ ወደውጭ ይላኩ የነበሩ ናሙናዎችን ለማስቀረት ተጨማሪ የመመርመሪያ መሳሪያዎች በግዥና  በእርዳታ በማስገባት ጫናውን መቀነስ እንደተቻለ አመልክተዋል።

በዚህም የመመርመር አቅምን ማሳደግና ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ማከናወን እንደተቻለ ነው የተናገሩት።

"ይሁን እንጂ አሁንም በአገሪቱ ያለው የመመርመር አቅም ካለው የህዝብ ቁጥር ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ ራሱን የቻለ ዘመናዊ የላቦራቶሪ ማዕከል መገንባት አስፈልጓል" ብለዋል።

ለዚህም ከዓለም ባንክ በተገኘ 150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ''ደረጃ-3 ባዮ ሴፍቲ ብሔራዊ ሪፈረንስ'' የተሰኘ ዘመናዊ የላቦራቶሪ ማዕከል ግንባታ ሥራ በኢኒስቲትዩቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በቅርቡ እንደሚጀመር አመልክተዋል።

ማዕከሉ ለምስራቅ አፍሪካ ጭምር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንደሚሆንም ተመልክቷል።

የዓለም ባንክ ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ ለግንባታው ብቻ እንደማይውል በአጽንኦት የገለጹት ዶክተር ኤባ፣ በክልል ያሉ የላቦራቶሪ ማዕከላትን በግብአት ለማጠናከርና አዳዲስ ለማቋቋም ጭምር እንደሚውል ጠቁመዋል።

የላቦራቶሪ ማዕከሉ ከኮቪድ-19 በተጨማሪ ሌሎች ወረርሽኞችንና የበሽታ አይነቶችን በፈጣን ሁኔታ ለመመርመር የሚያስችል ሆኖ እንደሚገነባና ዘመናዊ መሳሪያዎች እንደሚሟላለትም አመልክተዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘው እንደገለጹት በአገሪቱ ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊትና ከተከሰተ በኋላ በተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ስኬታማ ውጤት ተመዝግቧል።

ይሁን እንጂ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው መዘናጋት ስኬቱን ወደኋላ ከመጎተቱ ባለፈ የቫይረሱን የስርጭት መጠን እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል።

ዶክተር ኤባ አንዳሉት በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ 53 የኮቪድ-19 መመርመሪያ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን ተጨማሪ ዘጠኝ ላቦራቶሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀዋል።

ቫይረሱ ከመከሰቱ ከስምንት ወራት በፊት በተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማስፋትና ብሔራዊ የኮቪድ ግብረ ኃይል በማቋቋም መከላከልን መሰረት ያደረጉ ስራዎች በተሳካ ሁኔታ ሲከናወኑ ቆይተዋል።

ቫይረሱ ከተከሰተ ከ5 ወራት ወዲህም የመመርመር አቅምንና የማገገሚያ ማዕከላትን የማስፋት ሥራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ተቋማትና ግለሰቦች በኃላፊነት እንዲሰሩ በማድረግ በኩል ተከታታይነት ያለው ሥራ ሲሰራ እንደነበር ዶክተር ኤባ ጠቁመዋል።

በነሀሴ ወር የተካሄደው የንቅናቄ ዘመቻም ኮቪድ-19ኝን የመመርመር አቅምና በአገሪቱ የቫይረሱ ስርጭት ያለበት ወቅታዊ መረጃ የታወቀበት መሆኑን ገልጸዋል።

ንቅናቄው የክልሎችን አቅም ማጎልበት የተቻለበት እንደነበርም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።

ከእዚህ በተጨማሪ በቀጣይ በምን መልኩ መሰራት እንዳለበት ትምህርት የተወሰደበትና ምርመራን ለማጠናከር በቂ መረጃ የተገኘበት መሆኑን አመልክተዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በ2013 ዓ.ም በተቋም ደረጃ የሚደረጉ ተቋማዊ አሰራሮችን ማጠናከር ጨምሮ ምርመራዎችን በግል የጤና ተቋማት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ ይከናወናል።

መከላከልን መሰረት ያደረጉ ግብአቶች አቅርቦትና የአጠቃቀም አተገባበር ላይ በንቃት የመስራትና የማስተባበር ስራዎችም እንዲሁ።

በኮቪድ-19 ዙሪያ ተግባራዊ የሚደረጉ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎችም በአዲሱ ዓመት የሚተገበር መሆኑን ጠቁመዋል።

ኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን 1 ሚሊዮን 78 ሺህ 269 ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን 60 ሺህ 784ቱ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ 949 ሰዎች እንደሆኑም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 22ሺህ 667 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን 307 ሰዎች ደግሞ በጽኑ የህክምና ክፍል ውስጥ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም