ብፁዕ አቡኑ መርቆሪዎስ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዓቢይ ላስገኟቸው ስኬቶች ምስጋና አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ብፁዕ አቡኑ መርቆሪዎስ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዓቢይ ላስገኟቸው ስኬቶች ምስጋና አቀረቡ
አዲስ አበባ ጳግሜ 4/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ መርቆሪዎስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ላስገኟቸው ስኬቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፓትርያርኩ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በመገኘት መጪውን አዲስ ዓመት አስመልክተው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የእንኳን አደረስዎት ስጦታ አበረክተውላቸዋል፡፡
ፓትርያርኩ በፅሑፍ ባስነበቡት መልዕክታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች ለመገንዘብ ንጹህ ህሊና ብቻ በቂ ነው ብለዋል።
በተለይ ለሁለት ተከፍሎ የነበረው ሲኖዶስ ወደ አንድ በማምጣት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት ተይዘው የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ሃብቶች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለቤተክርሰቲያኒቱ እንዲመለሱ አድርገዋል ነው ያሉት።
በቤተ መንግስት በተገነባው የአንድነት ፓርክ በአፍሪካ ብዙም ባልተለመደ መልኩ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎችን እንዲታወሱ መደረጋቸው የሚደነቅ መሆኑንም ነው ፓትሪያርኩ የጠቆሙት።
በፓርኩ ውስጥ የቤተ ክርስቲያኗ ቅርሶች ለዓለም እንዲተዋወቁ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ''ኦርቶዶክስ ሀገር ናት'' በሚል አማናዊ ምስክርነት ለቤተክርስቲያን ያላቸውን አለኝታነት ማሳየታቸውንም ፓትርያርኩ አስታውሰዋል፡፡
አገር ችግር ላይ በወደቀችበት ወቅት በጥበብ በመምራት ረገድም ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም አቡኑ መርቆሪዎስ ገልጸዋል፡፡
ፓትሪያርኩ መጪውን የ2013 አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስጦታ አበርክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ቤተክርስቲያኗ ጸሎትና ምልጃ እያወጀች አገር ፀንታ እንድትቆም መስራቷንና እየሰራች መሆኗንም መስክረዋል፡፡
ሀገርና ህዝብ ሲፈተን የሚሸሽ ብዙ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዚህ አንጻር ሀገር በሚገጥማት ፈተና ሁሉ ጸንታ ሚናዋን እንድትወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የኮኮቦች ውበት ያለ ጨረቃ እንደማይደምቅ ሁሉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰብና ህዝቦች ያላቸው ውበት ጎልቶ የሚወጣው ሀገር በጸና መሰረት ላይ ስትቆም ነው ብለዋል።
ይህን ለማወቅ ደግሞ ሀገር የፈረሰባቸው ህዝቦች ህያው ምስክሮች መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።
በቀጣይ የተጀመረው መልካም ሥራ እንዲበዛና አገር እንድትበለጽግ የሃይማኖት አባቶች በፀሎት እንዲያግዟቸውም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ መርቆሪዎስ ለሰጧቸው እውቅና እና መልካም ምኞትም ምስጋና አቅርበዋል።