ተቋሙ በአዲሱ ዓመት የዜጎች ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥ ከህብረተሰቡ ጋር እንደሚሰራ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋሙ በአዲሱ ዓመት የዜጎች ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥ ከህብረተሰቡ ጋር እንደሚሰራ ገለጸ
አዲስ አበባ ጳግሜ 4/2012 (ኢዜአ)ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በ2013 የዜጎች ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥ ከህብረተሰቡ ጋር በላቀ የትብብር መንፈስ እንደሚሰራ ገለጸ።
አገልግሎቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በአዲሱ ዓመት ከተሰጠው ተልእኮ መነሻነት በአገር ሉአላዊነትና በዜጎች ደህንነት መረጋገጥ ጽኑ አቋምና ዝግጁ ነው።
ለዚህም ከመላው ህብረተሰብ ጋር በመተባበርም ሚናውን እንደሚወጣ ገልጿል።
በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት በአገርና በሕዝብ ላይ ደህንነት ስጋት የሚደቅኑ ችግሮች እንዳጋጠሙት ያወሳው ተቋም፤ይሁንና የመረጃና የጸጥታ መዋቅሮች ችግሮች ከፍተኛ ጉዳት ሳያስከትል ለመቀልበስ ሌት ተቀን በመስራታቸው አገራዊ ህልውናን ማስቀጠል ተችሏል ብሏል።
በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች እንዲፈጠሩ እንዲሁም በአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተሸረቡ የሽብር ሙከራዎችን ጨምሮ የህዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት እንዲደናቀፍ ሲጥሩ የነበሩ ሀይሎች ስጋት ደቅነው ነበሩ ብሏል።
ተቋሙ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር እንዲሁም ከመላው ህብረተሰብ ጋር በመተባበር ድርጊቱን ማክሸፍ እንደተቻለ ገልጿል።
በቀጣዩ ዓመት ተመሳሳይ ተግዳሮቶችን ለመፍጠር የሚሹ አካላትን ሴራ በተደራጀ የመረጃ ስራ ለማክሸፍ እንደሚሰራም አመልክቷል።
ከሌሎች የጸጥታና የመረጃ ተቋማት እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋርበ በመሆን ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት አገር እውን ለማድረግ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉንም ጠቁሟል።
አዲሱ ዓመት የደህንነት ስጋቶን በጥንቃቄና በከፍተኛ ርብርብ አስቀድሞ ለማክሸፍ እንደሚሰራም ገልጿል።
ተቋማሙ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የሆነ ፣ ሙያዊ ብቃት የተላበሰና ትውልድ ተሻጋሪ ተቋም ለመገንባት የጀመረውን የሪፎርም ስራም እንደሚያጠናክር ገልጿል።
የሕዝቡም ድጋፍ እንዳይለየው ጥሪውንም አቅርቧል።
አዲሱ ዓመትም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላምና የእድገት እንዲሆን ምኞቱን ገልጿል።